ህብረቱ አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በቋሚነት እንድትወከል ጥያቄ ሊያቀርብ ይገባል

111

ጂንካ፤ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ)፡ የአፍሪካ ህብረት አህጉሪቱ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በቋሚነት እንድትወከል ጥያቄ ሊያቀርብ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጂንካ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለጹ።

የጂንካ ዩኒቨርስቲ የስነ-ምግባርና የስነ-ዜጋ መምህር አንዷለም ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተቋቋመበት አላማ ይልቅ የምዕራባውያንን ሀገራት ፍላጎት ማስፈፀሚያ ሆኗል።

ድርጅቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ሁሉንም ሀገራት በእኩል ዓይን ከማየት ይልቅ ለድርጅቱ በጀት በመመደብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ምዕራባዊያን ሀገራትን ጥቅም ለማስከበር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ለድርጅቱ አመታዊ በጀት 22 በመቶውን ድርሻ ለምታበረክተው አሜሪካ የፈላጭ ቆራጭነት ሚና መሰጠቱን በአብነት ጠቅሰዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተመሰረተው መንግስት አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት እንደፈለጉ የሚጠመዝዙትና ጥቅማቸውን የሚያስከብር ተላላኪ መንግስት አለመሆኑ እንዳስቆጫቸው ተናግረዋል።

በተለይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይዘው የተነሱት "ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" የተሰኘው የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤና በምስራቅ አፍሪካ የፈጠሩት ሰላም ሀገራቱን ማስደንገጡን ጠቁመዋል።

"እሳቤው በአፍሪካ ላይ ዳግም ዘመናዊ ባርነት ለመጫንና አፍሪካን ለመቀራመት እንዲሁም ጂኦ ፖለቲካውን በበላይነት ለመቆጣጠር የወጠኑትን ሴራ ማክሸፍ ችሏል" ያሉት ምሁሩ ይህም ሀገራቱን በኢትዮጵያ ላይ ጥርስ እንዲነክሱ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያዊያንን አንገት ለማስደፋትና ኢትዮጵያን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መቀጣጫ ለማድረግ ፕሮጀክት ተቀርፆ ሀገር የማፍረስ ሴራው በአንዳንድ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን አጋፋሪነት ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉንም ምሁሩ አስገንዝበዋል። 

ምዕራባውያን ሀገር የማፍረስ ሴራቸውን ተፈፃሚ ለማድረግና በሰብዓዊ መብቶች ሽፋን ፈርጣማ ክንዳቸውን በኢትዮጵያ ላይ ለማሳረፍ እየሰሩ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ የጂንካ ዩኒቨርስቲ የህግ ምሁር ተሻለ ሻምበል ናቸው።

ቀደም ሲል በተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና በኢሰመኮ የወጣውን ሪፖርት የፀጥታው ምክር ቤት በድጋሚ የማጣራት ስራ እንዲሰራ ያስተላለፉት ውሳኔም የዚሁ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ዳግም  ጥናት እንዲካሄድ የፈለገበት ምክንያት በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሟል በማለት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ በሀሰት የጀመሩትን ክስ ለማጠናከርና ሀገር የማፈራረስ ሴራቸውን ለማሳካት መሆኑን ጠቁመዋል።

"የአለም ህዝብ እጣ ፈንታ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አምስት ቋሚ አባላት ብቻ ሊወሰን አይገባም" ያሉት የህግ መምህሩ "አፍሪካም እንደ አህጉር በቋሚ ኮሚቴው ውስጥ መካተት አለባት" ሲሉ አመላክተዋል።

የአፍሪካ ሀገራት በተናጠል ሳይሆን በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት ጥያቄውን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማቅረብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም