ከዳያስፖራው ወደ አገር ቤት የሚላከውን ገንዘብ ለማሳደግ ቀልጣፋ የፋይናንስ ሥርዓት ያስፈልጋል

64

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ) ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት የሚልከውን ገንዘብ ለማሳደግ መንግሥት ቀልጣፋ የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል ሲሉ የኢኮኖሚ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሙላቱ ፍቃዱ ገለጹ።

በደቡብ አፍሪካ የሱዋኔ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ፕሮፌሰር ሙላቱ ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት የሚልከው ገንዘብ ሕጋዊ ሥርዓትን መከተል አለበት ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከውጭ የሚላከው ገንዘብ /ሬሚታንስ/ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ዳያስፖራው ይህን በመገንዘብ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ፕሮፌሰሩ በእስያ የሚገኙ አገራት ከአጠቃላይ ምርታቸው ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ከውጭ አገር በሚገባ ገንዘብ እንደሚያገኙ ለአብነት ጠቀሰዋል።

በመሆኑም ከሬሚታንስ የሚገኝ ገቢ ለኢትዮጵያም እንደ ተጨማሪ የኃብት ማሰባሰቢያ ተደርጎ መወሰድ አለበት፤ መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም ዳያስፖራው ገንዘቡን ያለምንም ችግርና ቅድመ ሁኔታ ወደ አገር ቤት እንዲልክ ለማድረግ ቀልጣፋ የገንዘብ ፍሰት መኖር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል የአገሪቷን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት በቀጣናው ከሚገኙ ጎረቤት አገራት ጋር ሁለንተናዊ ትስስር ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በማንኛውም የልማትና የእድገት እንቅስቃሴዎች ከአፍሪካ በተለይም ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር ያስፈልጋልም ብለዋል።

ዳያስፖራው ባለፉት ሶስት ዓመታት በአማካይ 3 ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ ወደ አገር ውስጥ መላኩን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም