ለህልውና ዘመቻው እየተደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ዩኒቨርሲቲው

180

ደብረ ማርቆስ ፣ ታህሳስ 14/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበር እየተካሄደ ላለው የህልውና ዘመቻ እየተደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ድርቧ ደበበ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያን ለማፍረስና ትውልድ ለማጥፋት የተነሳው አሸባሪው ህወሓት እስኪጠፋ ድረስ ተቋሙ እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።

አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን የማፍረስ እንዲሁም ታሪክና ትውልድ የማጥፋት አላማ ይዞ መነሳቱን  ጠቁመው፣ አሸባሪው አሁን ላይ ህልሙ በጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ቅዥት እንደሆነበት ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት ዳግም ለህዝብና ለአገር ስጋት በማይሆንበት ደረጃ እስኪደርስ ዩኒቨርሲቲው ለህልውና ዘመቻው በስንቅ ዝግጅትና በሌሎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት ከህዳር 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ የስንቅ ዝግጅት 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት ደረቅ ስንቅ ተዘጋጅቶ በወሎና በሌሎች ግንባሮች ለተሰለፉ የፀጥታ ሀይሎች እየቀረበ ይገኛል።

“ከተዘጋጀው ስንቅ ውስጥ እስከሁን 110 ኩንታሉ እንዲሁም 5 ሺህ የመኝታ ፍራሽ ወደ ግንባር መላኩን ” አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በግንባር ለሚገኘው የፀጥታ ሃይል ተጨማሪ ስንቅ እየተላከ መሆኑን ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከስንቅ ዝግጅት እና አቅርቦት በተጨማሪ ሠራተኞቹን በማስተባበር ለ14 የዘማች ቤተሰቦችና ሁለት አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ከ11 ነጥብ 5 ሄክታር በላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን አስታውቀዋል ።

የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ብሩክ አብዩ በበኩላቸው እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት “እኔ ያልመራኋት አገር ትውደም” በሚል ተነሳስቶ እየፈፀመ ያለው ግፍ በታሪክ አይረሳም።

“አገርን ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የድርሻዬን እየተወጣሁ ነው” ያሉት መምህሩ፣ ኢትዮጵያን ከወራሪው ሀይል ነጻ ለማድረግ የማይተካ ህይወቱን እየከፈለ ላለው መከላከያ ሠራዊት የወር ደመወዛቸውን መለገሳቸውን ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ በህልውና ዘመቻው ላይ ማህበረሰቡ የተሻለ ግንዛቤ ኖሮት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ በወረዳዎች በመዘዋወር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራታቸውን ገልጸዋል።

በስንቅ ዝግጅትም ሆነ በሰብል ስብሰባ ሥራ በመሳተፍ የኋላ ደጀንነታቸውን እያረጋገጡ መሆኑን የገለጹት መምህሩ ድጋፋቸውን እስከ ድል ማግስት እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

“አገር ከሌለ በሰላም ወጥቶ መግባትም ሆነ ሰርቶ መብላት አይኖርም” ያሉት ደግሞ 

በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ማደሪያ ሕንጻ አገልግሎት ሠራተኛ አቶ ተስፋዬ አሻግሬ 

ናቸው።

“አገር ከሁሉም በላይ ናት በሚል  አብዛኛው ጊዜዬን ለህልውና ዘመቻው  በድጋፍ ዝግጅት ተግባራት እያሳለፍኩ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።