ህወሀት የፌዴራል ስርዓቱን ልዩነቶችን ለማስፋትና ለመለያየት በር መክፈቻነት ተጠቅሞበታል-ምሁራን

71

አዳማ፣ ታህሳስ 14/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሀት የፌዴራል ስርዓቱን ለህዝቦች እኩልነትና አንድነት ሳይሆን ለልዩነቶች ማስፍፊያና ለመለያየት በር መክፈቻ በማድረግ ለራሱ ዓላማ ማስፈፀሚያ ተጠቅሞበታል ስሉ ምሁራን አመለከቱ።

የህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምሮ ማእከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሃይለየሱስ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት 27 ዓመታት ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓቱን ከአንድ ፓርቲ ህወሃት ጋር በማቆራኘት የቡድን ዓላማ ማስፈፀሚያ አድርጎት ቆይቷል። 

"ቡድኑ ስርአቱን በህዝቦች መካከል ልዩነቶች እንዲሰፉ፣ለመለያየት በር እንዲከፈትና መጠራጠር እንዲነግስ በማድረግ ጭምር ተጠቅሞበታል" ብለዋል።

የህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓቱ በራሱ ችግር አይደለም፤ ማህበረሰባችንም የመለያየት ፍላጎት የለውም፤ ያሉት ዶክተር ሃይለየሱስ "በስልጣን ላይ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው ቡድን ህዝቦች ስለ ፌዴራል ስርዓቱ በትክክል እንዲገነዘቡ ከመስራት ይልቅ ልዩነቶችና ጥላቻ እንዲሰፋ ሲያስተምር ነበር" ብለዋል።

አሁን ላይ በህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም አተገባበርና አረዳድ ላይ ያለውን ተግዳሮት ለመቅረፍ በህገ መንግስት አስተምሮ ዙሪያ በርካታ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

"ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ለእንደኛ ሀገር ባለ ብዙ ማንነቶችና ልዩነቶች ሀገር ተፈጥሯዊና ትክክለኛ አማራጭ ቢሆንም በስርዓቱ አተገባበርና አያያዝ ላይ ችግር ነበር" ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት መምህርና ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ግዛቸው ተሾመ ናቸው። 

"እኛ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶችና የጋራ ማንነቶች አሉ፤ ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓቱ አማራጭ የሌለው ነው" ያሉት ዶክተር ግዛቸው ኢትዮጵያዊያን በአንድ መርከብ ላይ ያለን ህዝቦች ነን፤ አንዱ አንዱን እየጠበቀ መሄድ ካልቻልን በሚከፈተው ሽንቁር ሁላችንም እንሰምጣለን" ብለዋል።

በተለይ ህወሀት ለማንነት የተሰጠው ሚዛን በዋናው ኢትዮጵያዊ ምሰሶ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲፈጥርና ወደ ታች እንዲጎትተን አድርጓል" ሲሉም ተናግረዋል።

እኔ ኦሮሞ ልሆን እችላለሁኝ ፣ ኦሮሞነቴ ግን ከኢትዮጵያዊ ማንነቴ ጋር መጋጨት የለበትም" ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ህወሃት የብሔሮች ማንነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር እንዲጋጭና ሀገራዊ አንድነት እንዲዳከም ሲሰራ እንደነበር አስታውሰዋል።

"የነበረው ችግር የህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ስርዓት መከተላችን ሳይሆን ስርዓቱን ከህገ መንግስታዊ ዓላማ ውጭ ለፖለቲካ ፍላጎት ማሳኪያ የተገበርንበት ሂደት ነው" ብለዋል።

በዚህም በኢትዮጵያዊነት ላይ የተወሰነ መዛባት እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቅሰው ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም መከተላችን ከሀገራችን ተፈጥሯዊ ሁኔታ አንፃር አማራጭ እንጂ ችግር አለመሆኑን አስገንዝበዋል።

"በስርዓቱ አተገባበር ላይ ለቡድኑ ፖለቲካ ማስፈፀሚያ ተደርጎ እንጂ ብዙ ቋንቋ፣ሃይማኖት፣ብሔርና ማንነቶች ላሉዋት ኢትዮጵያ ሁሉንም በእኩልነት የሚያሳትፍና የሚያስተናግድ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ወሳኝ ነው" ያሉት ደግሞ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሶፊያ ይመር ናቸው። 

"በአተገባበር ወቅት ሃይማኖቶች፣ብሔሮችና ሌሎች ማንነቶችን የሚያስቀይም ተግባር ነበር፤ እኩል በሆነና ሁሉንም ባከበረ መልኩ አልተተገበረም" ብለዋል።

"የፌዴራል ስርዓቱ ያስፈለገው ለሀገር ሰላም፣ልማትና እድገት ብሎም ለህዝቦች አብሮ መኖር እንጂ ለመለያየትና ክፍፍል እንዲኖር አይደለም" ያሉት መምህርት ሶፊያ "ሁሉም የራሱ ማንነት ተከብሮለት በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ  ተባብረን መስራት አለብን" ሲሉ አመልክተዋል።

"የክልል መንግስታት ግንኙነት ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ባከበረ መልኩ መጠናከርና ክልሎች በህዝብ ጥቅምና በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ ተባብረው በመሰራት ችግራችንን መፍታት አለብን" ሲሉ መምህር ሶፊያ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም