ጤና ሚኒስቴር የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ጥራቱን ጠብቆ ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል የቃልኪዳን ሰነድ ይፋ አደረገ

104

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ)  ጤና ሚኒስቴር በ2030 የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ ጥራቱን ጠብቆ ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል የቃልኪዳን ሰነድ ይፋ አደረገ።

የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የቃል ኪዳን ሰነዱ ዛሬ ይፋ ሆኗል።

ዶክተር ሊያ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በየአመቱ የሚመዘገበው የእናቶች ሞት እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም ከ100 ሺህ እናቶች 401 የሚሆኑት በወሊድና ከወሊድ ጋር ተያይዞ ለሕልፈተ-ሕይወት ይዳረጋሉ።

በመሆኑም የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የቤተሰብ ዕቅድ ሚናው ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

መንግስት ለቤተሰብ እቅድ በጀትን በማሳደግ የጤና ተቋማት አገልግሎት ጥራት ማስጠበቅ እና በተቋማቱ ግብአት በማሟላት ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው የቃልኪዳን ሰነድም የቤተሰብ እቅድን በ2030 በታሰበው ልክ ለማሳካት ቃል የሚገባበት ነው ብለዋል።

በ2030 ከ18 አመት በታች ያሉ ልጆች እርግዝና አሁን ካለበት 13 በመቶ ወደ 3 በመቶ፣  የቤተሰብ እቅድን እየፈለጉ ማግኘት ያልቻሉትን ደግሞ አሁን ካለበት 22 በመቶ ወደ 17 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም