ወደ አገር ቤት የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅተናል- በሀዋሳ ሆቴሎችና ሪዞርቶች

108

ሃዋሳ፣ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር ቤት የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በጥሩ መስተንግዶ ለመቀበል ዝግጅት ማድረጋቸውን በሃዋሳ ከተማ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ገለጹ።

ለእንግዶች የአገልግሎት ክፍያ የ30 በመቶ ቅናሽ ማድረጋቸውን ባለቤቶቹ ለኢዜአ አስታውቀዋል።

በሀዋሳ ከተማ ከሚገኙ የሆቴል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል የሮሪ ሆቴል ኦፕሬሽናል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ገደፋው እንዳሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ያስተላለፉት ጥሪ የተለያዩ በጎ ተፅዕኖዎች አሉት።

በተለይም የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ከፍ ያለ መሆኑን አመልክተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያ ባህልና ቤተሰባዊ አቀባበል ተቀብለው ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም የሲዳማን ቱባ ባህል የሚገልጹ የምግብ፣ የመስተንግዶ እና ሌሎች ዝግጅቶችን ማድረጋቸውን ነው አቶ ሙሉ ቀን ያስታወቁት።

እንደ አቶ ሙሉቀን ገለጻ ሆቴሉ ለአገልግሎት ከሚያስከፍለው የ30 በመቶ ቅናሽ በተጨማሪ፣ ከባንኮች ጋር የሥራ ግንኙነት በማጠናከር ለእንግዶች ምቹና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል።  

ይህም ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጥሬ ገንዘብ ይዘው መምጣት ሳይጠበቅባቸው ክፍያዎችን በቀላሉ እንዲፈፅሙ የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የሆቴሉ ሠራተኞች ሙያዊና ሥነ-ልቦናዊ ዝግጅት እንዲያደርጉም ከወዲሁ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ከቱሪዝም ዘርፍና ከሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ሙሉቀን፣ የኮቪድ-19 መከላከያ መመሪያዎችን በሚገባ ተግባራዊ እንደሚያደርጉም አስረድተዋል።

የሌዊ ሪዞርትና ስፓ ኦፕሬሽናል ሥራ አስኪያጅ አቶ ይበሉ አለነ በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሠረት የገናን እና ጥምቀት በዓላትን ለማክበር ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ እንግዶች ያማረና የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የተሻለ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

"እንግዶቻችንን መቀበል የምንጀምረው ከአየር ማረፊያ ጀምሮ ነው" ያሉት አቶ ይበሉ፣ በሪዞርቱ በሚኖራቸው ቆይታም፣ በሃዋሳ የሚገኙ ሁሉንም የቱሪስት መዳረሻዎች በህብረት እንዲጎበኙ ከነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት ጋር ማመቻቸታቸውን ገልጸዋል።

በሀዋሳ ሐይቅ ላይ ነፃ የጀልባ ሽርሽርን ጨምሮ በሪዞርቱ የሚሰጡ ሙሉ አገልግሎቶች ላይ የ30 በመቶ ቅናሽ ማድረጋቸውን አቶ ይበሉ ተናግረዋል።

አቶ ይበሉ እንዳሉት ለእንግዶቹ በሪዞርቱ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች በተጓዳኝ በሃዋሳ ከተማና አካባቢው ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል።

ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ሠላማዊና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ከሃዋሳ ከተማ አስተዳደርና ከሲዳማ ክልል የሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የእንግዶች መዳረሻዎችን ዝግጁ ከማድረግ አኳያ ከቱሪዝም ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብረው እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል በላይነህ ናቸው።

ኃላፊው እንዳሉት በሃዋሳ ከተማ ከ16 በላይ ባለ ኮኮብ ሆቴልና ሪዞርቶች የሚገኙ ሲሆን በአቅራቢያ ባሉት ከተሞችም ለእንግዶች ምቹ የሆኑ ሎጆችና የቱሪስት መዳረሻዎች ይገኛሉ።

"እንግዶች በሚቆዩባቸው በነዚህ መዳረሻዎች ላይ የሲዳማ ክልልን ብሎም እንደ ሀገር የኢትዮጵያን ገፅታ ለማስተዋወቅና ለመገንባት ይሰራል" ብለዋል።

ለሀገራዊ ጥሪ በጎ ምላሽ ለመስጠት ከውጭ ለሚመጡ እንግዶች ተገቢውን አቀባበል ከማድረግ ባለፈ በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ዝግጅት መደረጉን አቶ ሳሙኤል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም