በዚህ የችግር ወቅት የኢትዮጵያዊያን የመረዳዳት ባህል ጎልቶ ወጥቷል - ዶክተር ይልቃል ከፋለ

127

ባህር ዳር ፣ ታህሳስ 13/2014(ኢዜአ) ''አሸባሪው ህወሓት በፈፀመው ወራራ ምክንያት ክልሉ ችግር ውስጥ በወደቀበት በዚህ የችግር ወቅት የኢትዮጵያዊያን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ጎልቶ ወጥቷል'' ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና ህዝብ ለተፈናቀሉ ወገኖች የ15 ሚሊዮን የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አድርጓል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በድጋፉ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን በክልሉ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች የክፋትና የጭካኔ ጥጉን አሳይቷል።

"በዚህም ንፁሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ ንብረት አውድሟል፣ ዘርፏል፣ ዘግናኝ የሆነ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችንም ፈፅሟል" ብለዋል።

በርካቶችን ደግሞ ከቤት ንብረት በማፈናቀልና በማጎሰቆል ለችግር መዳረጉን ነው የገለጹት።

በሽብር ቡድን ወረራ ምክንያት የክልሉ ህዝብ ችግር ሲደርስበት ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በሞራልና ሌሎች የተለያዩ ድጋፎችን ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

"ይህም በችግር ወቅት መላው ኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ የመረዳዳት፣ የመተጋገዝና የመደጋገፍ ባህላችን ጎልቶ እንዲወጣ አድርጓል" ብለዋል።


''ኢትዮጵያዊነት ለሁሉም የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ጥላ ነው'' ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የአብሮነትና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የምንችልበት መገለጫ እንደሆነም አመልክተዋል።


የድሬዳዋ አስተዳደርና ህዝብ  በክልሉ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸው የኢትዮጵያዊነትን የመደጋገፍና አብሮነትን የሚያረጋግጥ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአሸባሪው ህወሓት ወረራ በተፈፀመባቸው አካባቢዎችም መላ ኢትዮጵያዊያንና የዲያስፓራው ማህበረሰብ  ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

ለተደረገው ድጋፍም ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳድርና ህዝብ  ምስጋና አቅርበው፤ በቀጣይም የፈረሱ ተቋማትንም ሆነ ተፈናቃዮችን መልሶ በማደራጀትና ለማቋቋም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው "ክልሉ የደረሰበት በደልና ጉዳት የድሬዳዋ ህዝብም በደል ነው" ብለዋል።

"በዚህም በአሸባሪውና ወራሪም ህወሓት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች የድሬዳዋ አስተዳደርና ህዝብ  ከጎናቸው ይቆማል" ሲሉም አረጋግጠዋል።

አስተዳደሩ ከአማራ ክልል ህዝብ ጋር በወንድማማችነት የተመሰረት ግንኙነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከንቲባው ተናግረዋል።

አስተዳደሩ ካደረገው ድጋፍ ባሻገር የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚሰራው ስራ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።


አስተዳደሩና ህዝብ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ፣ 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው አልባሳትና የምግብ እህል ድጋፍ ተደርጓል።

ድጋፉንም  ከንቲባ ከድር ጁሃርን ጨምሮ የአስተዳደሩ የሥራ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች እና ኡጋዞች በባህር ዳር ከተማ ተገኝተው ለክልሉ አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም