የሆስፒታል ገንዘብ ተቀባይ ሰራተኛ መስሎ ከታካሚዎች ገንዘብ በመቀበል ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ ተቀጣ

63

ጭሮ፣ ታህሳስ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጭሮ አጠቃላይ ሆስፒታል ገንዘብ ተቀባይ ሰራተኛ መስሎ ከታካሚዎች ገንዘብ በመቀበል ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በእስራትና ገንዘብ መቀጣቱን የጭሮ ወረዳ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

የፍርድ ቤቱ ዳኛ ኤልሳቤት ታደሰ  ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተከሳሹ ሮባ ዳንዱ ራሱን የሆስፒታሉ ሰራተኛ በማስመሰል የላቦራቶሪና የካርድ ማውጫ የገንዘብ ክፍያ እየተቀበለ እንደሚሰወር በሰው ምስክርና በፖሊስ ምርመራ ተረጋግጦበታል፡፡

በሁለት የተለያዩ መታወቂያዎች እየተጠቀመ በማጭበርበር ወንጀል የተከሰሰው ግለሰቡ ድርጊቱን በተመሳሳይ ለመፈጸም ታህሳስ 04 ቀን 2014 ዓ.ም ሲሞከር እጅ ከፍንጅ ተደርሶበት እንደታየዘ  አስረድተዋል።

በተለይ "ከገጠር አካባቢ የሚመጡትን ታካዎችን ጉዳያችሁን ሳትጉላሉ በአጭር ጊዜ አስጨርስላችኋለሁ" በማለት እያጨበረበረ ከአንድ ታካሚ 300 ብር ይቀበል እንደነበርና በተያዘበት ዕለትም ከስድስት ታካሚዎች ገንዘብ ሲቀበል እንደተደረሰበት ተመልክቷል፡፡

በዐቃቤ ሕግ ከሳሽነት ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የጭሮ ወረዳ ፍርድ ቤት ታህሳስ 11 ቀን 2014 ዓ.ም  በዋለው ችሎት በአንድ ዓመት ከስድስት ወር እስራትና 2 ሺህ ብር እንዲቀጣ መወሰኑን ዳኛዋ አስታውቀዋል።  

የጭሮ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሚካኤል ዳኜ በበኩላቸው፤ ግለሰቡ በተደጋጋሚ ታካሚዎችን ሲያጭበረብር እንደነበር በመረጃ መረጋገጡ ተናግረዋል።

ሆስፒታሎችም ሆኑ ሌሎች በርካታ የተገልጋይ ቁጥር ያላቸው ተቋማት መሰል የማጭበርበር ወንጀሎችን ለመከላከል ለሰራተኞቻቸው የደረት ባጅ፣ የካርድና ክፍያ ጉዳዮች በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቢያደርጉ ችግሩን መፍታት  እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም