የበቃ ዘመቻ በአፍሪካና በጥቁር ህዝቦች ላይ የተፈፀመው ግፍ “መቼም አይደገምም” ወደሚል የትግል ምዕራፍ ተሸጋግሯል

287

ታህሳስ 13/2014(ኢዜአ) የበቃ ዘመቻ በአፍሪካና በጥቁር ህዝቦች ላይ የተፈፀመው ግፍ “መቼም አይደገምም” ወደሚል የትግል ምዕራፍ መሸጋገሩን የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ተናገሩ።

በውጭ ሀገራትና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካንና የአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራትን የውጭ ጣልቃ ገብነት በቃ በማለት የትግል ዘመቻ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ የበቃ ዘመቻን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የበቃ ዘመቻ በዲፕሎማሲ፣ በተቃውሞ ሰልፎች፣ በዲጂታል የመረጃ ጦርነት እና በገንዘብ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊ የትም ቢሄድ ኢትዮጵያዊ ነው የሚሉት ዲያቆን ዮሴፍ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሀገሩን መነካት በመቃወም የአውሮፓና አሜሪካ አደባባዮችን በተቃውሞ ማጥለቅለቁን ተናግረዋል።

አንዳንድ ምዕራባውያን ኢትዮጵያን እንደ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ሶማሊያና አፍጋኒስታን ለማድረግ ሲነሱ፥ ኢትዮጵያውያን ሀገሬን አትንኩ በቃችሁ በሚል የአባቶቻቸውን የጀግንነት ታሪክ የፈፀሙ ልዩ ህዝብ ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫናና ጣልቃ ገብነት የበቃ ዘመቻ በማጠናከር አውሮፓውያን በተለይም አንዳንድ ምዕራባውያን በአፍሪካ ላይ በቅኝ ግዛት የፈፀሙትን ግፍ ዳግም በእጅ አዙር እንዳይፈፅሙት “መቼም አይደገምም” ወደሚል የትግል ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑንም ነው የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የተናገሩት።

አይሁዶች ስድስት ሚሊየን ህዝብ ከተጨፈጨፈባቸው በኋላ መቼም አይደገምም ብለው በመነሳት ራሳቸውን ማስከበራቸውን ያነሱት ዲያቆን ዮሴፍ ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውያንም በቃችሁ፤ መቼም አይደገምም #Never Again ማለት አለባቸው ብለዋል።

የተቃውሞ ንቅናቄው ኢትዮጵያን እና አፍሪካን የማያከብሩ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ የሚገቡ ፖለቲከኞችን በምርጫ ካርድ እስከመቅጣት የደረሰ እቅድ እንዳለውም ዲያቆን ዮሴፍ አብራርተዋል።

ለአብነትም በአሜሪካ ለተቃውሞ ወደ አደባባይ ከሚወጣው ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአሜሪካ ዜግነት ያለው በመሆኑ የመምረጥ መብት አለው፤ ይህ ደግሞ ያስፈራቸዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ችግር ተከትሎ ከጎኗ የቆሙ ወዳጆቿን እና ጠላቶቿን ለመለየት ችለናል ያሉት ዲያቆን ዮሴፍ፥ “አፍሪካውያን ወንድም እና እህቶቻችን ከጎናችን ተሰልፈዋል ” ብለዋል።

የበቃ ዘመቻ ንቅናቄው ከአፍሪካ አልፎ የጥቁሮች ሁሉ ትግል መሆኑን እያስተጋባን ነው ብለዋል።

እንደ ዲያቆን ዮሴፍ ገለጻ የበቃ እና መቼም አይደገምም ዘመቻውን ከጥቁሮች በተጨማሪ በአመለካከት ከሚደግፉ እና የማዕቀብ ተፅዕኖን ከሚቃወሙ የአሜሪካ ድርጅቶች ጋርም በጥምረት እየተሠራ ነው።

የበቃ ዘመቻን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የበርካታ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የቱርክ የቻይና እና የሩሲያ ባለስልጣናት መቀላቀላቸው ይታወሳል።