ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለመከላከያ ሆስፒታል የ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የህክምና ቁሶች እና መድሃኒቶችን ድጋፍ አደረገ

238

ሐረር ፤ ታህሳስ 13/2014(ኢዜአ) ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሀገር መከላከያ የምስራቅ ዕዝ ደረጃ ሶስት ሪፈራል ሆስፒታል 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ የህክምና ቁሶችን እና መድሃኒቶችን ዛሬ ድጋፍ አድርጓል።

በድጋፉ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ እንደገለጹት፤ በሀገር ላይ ከውጭ እና ከውስጥ የተቃጣውን ጦርነት ለመመከት ዩኒቨርሲቲው ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል።

ከዚህ ቀደም የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና አስተዳደር ሰራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን እንዲሁም ከተቋሙ የውስጥ ገቢ ጨምሮ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በምስራቁ የሀገሪቱ ከፍል ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የህክምና አገልግሎት፣አልባሳት እና ህሙማን ተኝተው የሚታከሙበት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም አውስተዋል።


በዛሬ ዕለት ለመከላከያ ሆስፒታል ያደረጓቸው የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች፣ መድሃኒቶች እና የጽዳት መጠበቂያ ቁሶች ደግሞ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል።


ሀገርን ለማዳን የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ጀማል አስታውቀዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የምስራቅ ዕዝ ጤና መምሪያ ሃላፊ ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል ክበበው ህጉ በበኩላቸው፤ የህግ ማስከበሩ እንቅሰቃሴ ከተጀመረ አንስቶ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይ ዩኒቨርሲቲው ሐረር ከተማ በሚገኙት የድንገተኛ ህክምና መስጫ ማዕከል እና ህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሰራዊቱ በሚገባ ህክምና እየሰጡ ነው ብለዋል።

ዛሬ የተለገሰው የህክምና ቁሳቁስ፣ መድሃኒት እና ንጽህና መጠበቂያ በአስፈላጊ ወቅት የተደረገና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።