'የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የአገር ቤት ጉዞ ጥሪ' ኢትዮጵያ የሰላም አገር መሆኗን የምናሳይበት ነው

70

ታህሳስ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) 'የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የአገር ቤት ጉዞ ጥሪ' ኢትዮጵያ የሰላም አገር መሆኗን የምናሳይበት ነው ሲሉ የኡጋንዳ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ሊቀ-መንበር ዶክተር ሩጋራማ ዳንኤል ገለጹ።

የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ አፍሪካውያን የአፍሪካ ማዕከልና የሰው ዘር መገኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ መምጣት አለባቸው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በውጭ አገር የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የኡጋንዳ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ሊቀ-መንበር ዶክተር ሩጋራማ ዳንኤል የምዕራቡ ዓለም አንዳንድ አገራትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው ኢትዮጵያ የደህነት ስጋት ያለባት አገር ናት በማለት ዓለምን ለማሳሳትና በዜጎች ላይ ፍርሃት ለመፍጠር እየሰሩ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ምዕራባውያን አገራት ዜጎቻቸው እንዲወጡ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ እንደነበረ አስታውሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ ጥሪ  አንዳንድ ምዕራባውያን እንደሚሉት ሳይሆን ኢትዮጵያ የሰላም አገር መሆኗን የምናሳይበት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብለዋል።

አፍሪካውያንና በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ወዳጆች ጥሪውን ተቀብለው በመምጣት የምዕራባውያን አገራትን ሴራ ማክሸፍ እንዳለባቸው ነው ዶክተር ሩጋራማ የገለጹት።

እሳቸውን ጨምሮ የኡጋንዳ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አባላት ጥሪውን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡና ሌሎች የኡጋንዳ ዜጎች ጥሪውን እንዲቀላቀሉ የማስተባበር ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ሊቀ-መንበሩ አመልክተዋል።

የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ አፍሪካውያን የአፍሪካ ማዕከልና የሰው ዘር መገኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ መምጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

አፍሪካውያን ወደ እናታቸው ቤት መጥተው በመሰባሰብ አንድ ቤተሰብና ማህበረሰብ መሆናቸውን በተግባር በማሳየት ጠላቶቻችንን ማሳፈር ይጠበቅብናል ብለዋል።

ጥሪው የዓለም ማህበረሰብ ተቀብሎት ሊቀላቀለው የሚገባ መልካም ሀሳብ እንደሆነም ዶክተር ሩጋራማ አክለዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም