የ'ታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት' ንቅናቄ ቱሪዝሙን በማነቃቃት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ እመርታ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል

87


አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 13/2014 (ኢዜአ)  የ'ታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት' ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ እመርታ ትልቅ ተስፋ እንደሚኖረው በኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ የሚንቀሳቀሰው የሰሜን ኢኮቱርስ ባለቤት ማርኮ ዳጋስፐር ተናገረ።


ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የመጣው ጣሊያናዊው ማርኮ ዳጋስፐር፤ በኢትዮጵያ ውብ ባህልና ተፈጥሮ ተማርኮ ከኢትዮጵያዊት ሴት ትዳር መስርቶ ኑሮውን በአዲስ አበባ ካደረገ 7 ዓመታት ተቆጥረዋል።

'ሰሜን ኢኮቱርስ' የተሰኘ የቱሪስት ድርጅት በማቋቋምም በኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ነው።

ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ በባህላዊና ተፈጥራዊ ሀብቶች የታደለች መሆኗን፣ ማንም ሰው በፈለገው ስፍራ ያሻውን ሰርቶ መለወጥ የሚችልበት ትልቅ ጸጋ እንዳላትም ነው የመሰከረው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ያቀረቡት ጥሪ በኮቪድ-19 እና በግጭት ለተቀዛቀዘው የሀገሪቱ ቱሪዝም ትልቅ ተስፋ መፍጠሩን ገልጿል።

ከዚህ ባሻገር ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ እመርታ መልከ ብዙ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ነው የተናገረው።

ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዳያስፖራዎች በቆይታቸው ከሚገኝ የውጭ ምንዛሬ ባሻገር በዘላቂነት መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ የሚያደርጉበት ዕድል ይፈጠራል ብሏል ዳጋስፐር።

እናም የ'ታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት' እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ በእርግጥም የልጆቿን ድጋፍ በምትሻበት እንዲሁም ገና እና ጥምቀት በሚከበሩበት ወሳኝ ጊዜ የተወጠነ ሃሳብ ነው ብሏል።

ሀገራዊ ጥሪውን ተከትሎ የሌሎች ሀገራት ቱሪስቶችም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡና በሀገሪቱ ተዘዋውረው ጉብኝት እንዲያደርጉ መስራት ይገባል ብሏል።

ዓለምአቀፍ ተሪስቶች ጎንደርና ላሊበላን ጨምሮ በምሥራቅ፣ በምዕራብ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ተዘዋውረው ጉብኝት ማድረግ እንደሚችሉ ጠቁሞ፥ የእርሱ ድርጅት ለጎብኝዎች የ30 በመቶ የአገልግሎት ቅናሽ ማድረጉን አስታውቋል።

በመሆኑም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያን መጎብኘት የሚሹ እድልን በመጠቀም በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት በኢትዮጵያ ሀሴት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የሰሜን ኢኮቱርስ ባለቤቱ ማርኮ ዳጋስፐር ኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት ሰፍኖባት፤ የቀደመ የቱሪስቶች መዳረሻነቷ ተመልሶ ማየት እንደናፈቀም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም