በሐረሪ ክልል ባለፉት አምስት ወራት ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ባለፉት አምስት ወራት ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተሰበሰበ

ሐረር ፤ ታህሳስ 13/2014(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ያለፉት አምስት ወራት ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ለግብር አሰባሰብ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን የመለየትና መፍትሄ የመስጠት ስራም እየተካሄደ መሆኑ ተመላክቷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት አምስት ወራት የተሰበሰበው ገቢ ቀጥተኛና ቀጥታ ካልሆነ ታክስ፣ ታክስ ነክ ካልሆኑና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ነው።
በእነዚህ ወራት የተሰበሰበው ገቢ የዕቅዱን 95 ነጥብ 3 በመቶ ሲሸፍን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በ39 ነጥብ 4 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
በተለይ የተቀናጀ የግብር አሰባሰብ ስርዓት በመዘርጋቱና ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግብርን በወቅቱ የመክፈል ልምዱ መዳበር ለገቢው ማደግ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ በተመለከተ አሁንም ከገቢ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ የአፈጻጸም ችግሮች መኖራቸውንና ይህንንም ለመፍታት ቢሮው በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
በክልሉ ደረሰኝ ከመቁረጥ፣ ታክስ ከማጭበርበርና መሰል የግብር አሰባሰብ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ለግብር ከፋዩ ስልጠና በመስጠት ወደ አሰራር ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ግብር ለሀገር ልማት የህልውና ጉዳይ ነው የሚሉት በከተማው ቀበሌ 14 ልዩ ስሙ ካናል ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በአልባሳት ንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ምትኩ ታደሰ፤ የሚጠበቅባቸውን 18 ሺህ ብር ግብር በወቅቱ መክፈላቸውን ገልጸዋል።
አሁን ሀገር የገጠማትን ችግር በአሸናፊነት እንድትወጣ ለህልውና ዘመቻው በደጀንነት ካደረጉት ድጋፍ በተጨማሪ ግብራቸውን በአግባቡና በወቅቱ መክፈላቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በአትክልት ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ግርማ ውድነህ በበኩላቸው፤ ግብርን በአግባቡ መክፈል ከዜግነት ግዴታዎች ባለፈ የሀገር ወዳድ መገለጫ በመሆኑ ግብራቸውን በወቅቱ መክፈላቸውን ገልጸዋል።
ግብራቸውን በወቅቱ ከመክፈል ባለፈ መንግስት ሳይፈልግ ተገዶ ለገባበት የህልውና ዘመቻ የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
በቀጣይም ግብራቸውን በአግባቡ ከመክፈል ባለፈ በተለያየ መስክ ለሀገር የሚያደርጉተን አስተዋጽኦ እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
በሐረሪ ክልል በተያዘው የበጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።
ዕቅዱን ለማሳካትም ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በግብር አሰባሰብ ላይ የተጀመረውን የአቅም ግንባታ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አመልክቷል።