ደሴና ኮምቦልቻን ጨምሮ በ30 ከተሞች በአሸባሪው ቡድን የወደሙ የውሃ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ደሴና ኮምቦልቻን ጨምሮ በ30 ከተሞች በአሸባሪው ቡድን የወደሙ የውሃ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

ባህር ዳር፣ ታህሳስ 13/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በ30 ከተሞች ውስጥ በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ የውሃ ተቋማትን መልሶ በመጠገን ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረጉን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የወደሙ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ለማስጀመር 1 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አደም ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪ ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩ 82 ከተሞች ከ250 በሚበልጡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ላይ ዘረፋና ውድመት አድርሷል።
በተቋማቱ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይገለገል እንደነበር አስታውሰዋል።
የአሸባሪ ቡድኑ ወራሪ ሀይል የቧንቧና የኤሌክትሮ መካኒካል መለዋወጫዎችን፣ ፓምፖችና ጄኔሬተሮች እንዲሁም የውሃ ጥራት መፈተሻ መሳሪያዎችን ዘርፎ የተቀሩትን ማውደሙን ገልጸዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኘውን የክልሉን ብቸኛ ተንቀሳቃሽ የውሃ ጥገና አገልግሎት ወርክ ሾፕ ጭምር ማውደሙን አቶ አደም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የአራት ዞኖች የውሃ መምሪያዎችን ጨምሮ የ76 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ውሃና ኢነርጂ መምሪያዎችና ጽህፈት ቤቶችን መዝረፉንና ማውደሙን ተናግረዋል።
ከአሸባሪው ቡድን ነፃ በወጡ አካባቢዎች እስካሁን 53 የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተጠግነው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቁመው ለጥገናው 116 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አመልክተዋል።
ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞችን ጨምሮ በ30 ከተሞች ተጠግነው አገልግሎት በጀመሩት የውሃ ተቋማት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ተጠቃሚ መሆኑን አስታውቀዋል።
ቢሮው በሌሎች ከተሞች የወደሙና የተዘረፉ የውሃ ተቋማትን ሥራ ለማስጀመር በአራት ቀጠናዎች የባለሙያዎች ቡድን እያሰማራ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋማቱን መልሶ አገልግሎት ለማስጀመር እየተደረገ ባለው ጥረት ኢትዮጵያዊያን ትብብር እንዲያደርጉ ኃላፊው ጠይቀዋል።