አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት በሰብዓዊ መብት ስም በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና አፍሪካን ለመቆጣጠር ያለመ ነው

293

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 13/2014(ኢዜአ) ‘አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት በሰብዓዊ መብት ስም በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና አፍሪካን ለመቆጣጠር ያለመ ነው ሲል የታሪክ ምሁሩና ጋዜጠኛ ቶማስ ማውንቴን ተናገረ።

የታሪክ ምሁሩና ጋዜጠኛው ቶማስ ማውንቴን ለኢዜአ እንደገለጸው፤ አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ያለመ ነው።

ይህም አፍሪካን በተለይም ደግሞ የአፍሪካ ቀንድን ለመቆጣጠርና ስትራቴጂካዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር መሆኑን ገልጾ፤ ጉዳዩ ከሰብዓዊ መብት ጋር ግንኙነት የለውም ብሏል።  

አሜሪካ የቀይ ባህርና የባብል ማንድብ የባህር ወሽመጥ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት የሚጠቅሰው ቶማስ ማውንቴን፤ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገው ተጽዕኖ ይህንን ተጠቃሚነት ላለማጣት የሚደረግ ርብርብ መሆኑን ነው ያስረዳው።  

እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ “ይህ ግዛቴ ነው አይመለከታችሁም” በማለት እየተደረገባት ያለውን ጫና እየተቋቋመች መሆኑን ተናግሯል፡፡

ይህም ለአንዳንድ የምዕራባውያን አገራት ከፍተኛ ራስ ምታት መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ በአሸባሪው ሕወሓት የሥልጣነ ዘመን በምዕራብያኑ ተጽዕኖ ሥር ስትዳክር መቆየቷንም ነው ያስታወሰው፡፡   

ነገር ግን ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ እምቢተኝነት የአሸባሪው የሕወሓት አገዛዝን ሲገረስሰው በኢትዮጵያ የነበረው የምዕራባውያን ተጽዕኖ አብሮ መክሰሙን ተናግሯል።  

ይህንን ተከትሎ ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ አዲሱን የቅኝ ግዛት ለማንኮታኮት እየተከተለች ያለችው የነጻነት መንገድ አሳስቧቸዋል ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን ወደ እውነተኛ ነጻነትና አዲስ የማኅበራዊ ሥርዓት እያሸጋገሯት መሆኑንም ነው ያነሳው።