በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደሴ ዲስትሪክት ከሰማንያ በላይ ትራንስፎርመር በሽብር ቡድኑ ተዘርፏል

111

ታህሳስ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደሴ ዲስትሪክት ከሰማንያ በላይ ትራንስፎርመር በሽብር ቡድኑ ተዘርፏል።

በአማራ ክልል ከተዋቀሩ ስድስት ዲስትሪክቶች መካከል አንዱ የሆነው የደሴ ዲስትሪክት በስሩ 23 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት አሉት።

የደሴ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሀብቱ አበበ እንዳሉት፣ የአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎች በደረሱባቸው ቦታዎች ያሉ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የሽብር ቡድኑ በዲስትሪክቱ ዋና መስሪያ ቤት ያሉ ንብረቶችን የቻለውን ዘርፎ ቀሪውን ሙሉ በሙሉ አውድሞ መሄዱን ገልጸዋል።

ከከባድ ተሽከርካሪ ጀምሮ በማከማቻ ማዕከሉ ያሉ ንብረቶችን ዘርፎና አውድሞ ተቋሙን ባዶ አድርጎታል ብለዋል።

በደሴ ዲስትሪክት በዋናው የክምችት ማዕከል የሚገኙ በሚሊየን ብር የሚቆጠር ግምት ያላቸውን ከ80 በላይ ትራንስፎርመሮች እንደተዘረፉም ገልፀዋል።

የሽብር ቡድኑ የኢንዱስትሪ ማዕከል የሆኑት የደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች የመብራት እጦት እንዲገጥማቸው ለማድረግ የደሴን ሰብ ስቴሽን/ማከፋፈያ ጣቢያ በከባድ መሳሪያ መድፍ አውድሞታል ብለዋል።

በደሴ ዲስትሪክት ላይ የተፈጸመው ዘረፋና ውድመት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ሀብቱ ይሄንን በአዲስ መልክ ለማደራጀት እንገደዳለን ብለዋል።

በመሆኑም የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የፌደራሉ ጭምር ተቀናጅተው የሚፈቱት ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም