የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚመለከተው ኢትዮጵያዊያንን እንጂ የውጭ አገራትን ሊሆን አይገባም

182

ታህሳስ 13/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚመለከተው ኢትዮጵያዊያንን እንጂ የውጭ አገራትን ሊሆን እንደማይገባ ካናዳዊው ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ ተመራማሪው ጆን ፊልፖት ተናገሩ።

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ እያደረገ ያለው ጫና እና ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም የተጀመረው የዲፕሎማሲ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ ተመራማሪው ጆን ፊልፖት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ማንም አገር በሌላ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ መግባት የማይችል መሆኑ ይታወቃል።

በመሆኑም አንዳንድ የምዕራብ አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ምንም አይነት መብት የላቸውም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚመለከተው ኢትዮጵያዊያንን እንጂ የትኛውንም የውጭ አገራት ሊሆን አይገባም ብለዋል።

በተለይም አሜሪካና እንግሊዝ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በቅጡ ያውቃሉ ብለዋል።   

ይሁን እንጂ እውነታውን በቅጡ እየተረዱት በተቃራኒው በመቆም አሸባሪውን ህወሃት ደግፈው የቆሙ እንዳሉ ጠቅሰዋል።

እነዚህ አገራትና አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች የያዙት አቋም እርስ በእርሱ የሚቃረን እና እውነትን የካደ መሆኑን ጆን ፊልፖት ተናግረዋል።

በሕዝብ ድምጽ የተመረጠን መንግሥት እውቅና በመንፈግ እነርሱ ከያዙት አቋምና ፍላጎታቸው ጋር የመሰላቸው አሸባሪ ቡድን ጋር ወግነዋል ነው ያሉት።   

የአሜሪካን መንግስት ጨምሮ አንዳንድ የምዕራብ አገራት ዜጎቻቸውን ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ሲወተውቱ የቆዩትም ነባራዊ እውነታው ጠፍቷቸው ሳይሆን ሕዝቡ ፍርሃት ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።  

በአሁኑ ወቅት ጦርነት የተለያዩ መንገዶች አሉት ያሉት ተመራማሪው ዜጎቻቸው እንዲወጡ የሚያደርጉት ዘመቻም ሌላኛው የጦርነት አካል መሆኑን ገልጸዋል።   

በሌላ በኩል አገራቱ የአንድን አገር ምጣኔ ኃብት ለማዳከም የሚጠቀሙት ስልት ማዕቀብ መሆኑን ገልጸው አሜሪካም በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለች ያለው ይህንኑ ነው ሲሉ አብራርተዋል።  

እቅዱ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸው የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ እያደረገ ያለው ጫና እና ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም የተጀመረው የዲፕሎማሲ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

እርሳቸው ማዕቀብን የሚከላከል ተቋም ውስጥ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማዕቀብ ተግባራዊ እንዳይሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።