ኀብረተሰቡ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋምና የወደሙ ተቋማትን ለመገንባት በአንድነት መነሳት አለበት

58

አዲስ አበባ ታህሳስ 13/2014(ኢዜአ) ''ኀብረተሰቡ በጦርነቱ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋምና የወደሙ ተቋማትን ለመገንባት በአንድነት መነሳት አለበት'' ሲል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ በጦርነቱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ለችግር መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህም አልፎ በርካታ መስጊዶች፣ ቤተክርስቲያናት፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት መውደማቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በመሆኑም ኀብረተሰቡ በተለመደው መልኩ ለተፈናቀሉ ዜጎች ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ በማጠናከር ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የወደሙ ተቋማትንም መልሶ ለመገንባት ሕዝቡ መተባበር እንዳለበት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ አሳስበዋል።

ምክር ቤቱም በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ስልሳ ዜጎችን እየተንከባከበ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ ኮሚቴዎችን አዋቅሮና ለዚሁ ተግባር የሚሆን የሂሳብ ደብተር ከፍቶ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ መስጊዶች ድጋፍ ለማሰባሰብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር እድሪስ አክለውም ''ዛሬ የገጠመንን ፈተና በመተጋገዝ፣ በመረዳዳትና በመተሳሰብ ልናልፈው ይገባል'' ብለዋል በመግለጫው።

በተለይም ከአሻባሪው ቡድን ነጻ የወጡ አካባቢዎች የሽብር ቡድኑ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው፤ ዜጎች ወደ ቀዬያቸው ሲመለሱ ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም