ከመጪው የገና እና ጥምቀት በዓላት ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት የ5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ግዥ እየተከናወነ ነው

187

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 13/2014(ኢዜአ) ከመጪው የገና እና ጥምቀት በዓላት ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከውጭ ለማስገባት ግዥ እያካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት በዋናነት ለኢንዱስትሪ ምርት የሚሆኑ ግብዓቶችንና የፋብሪካ ምርቶችን የሚያቀርብ ድርጅት ሲሆን፤ በተጨማሪ ምግብና የምግብ ነክ ፍጆታዎችን ለኀብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ያደርጋል።

የድርጅቱ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ንጉሴ ገብረማሪያም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ በተለይ በአሁኑ ወቅት በዘይት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ክፍተት እንዳይፈጠር በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

ለአብነትም በተያዘው በጀት ዓመት መስከረም ወር 24 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከውጭ በማስገባት ለኀብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን አንስተዋል፡፡

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት መጪውን የገና እና ጥምቀት በዓላት ምክንያት በማድረግ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከውጭ ለማስገባት ግዥ እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በዋናነት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው ያስረዱት፡፡

መንግስት በአገር ውስጥ ያሉ ዘይት አምራቾችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱን ገልጸው፤ በዚህም አሁን ላይ በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች መነቃቃት እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአገር ውስጥ ያሉ ዘይት አምራች ድርጅቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም እስካሁን ባለው ሂደት በአገር ውስጥ ያለውን የዘይት ፍላጎት በማሟላት ረገድ ከ25 በመቶ ያነሰ ድርሻ እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡