የትግራይ ህዝብ አሸባሪውን ህወሓት በቃህ ሊለው ይገባል

251

አሶሳ፤ ታህሳስ 13/2014 (ኢዜአ)፡ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጎን በመቆም አሸባሪውን ህወሓት በቃህ ሊለው የሚገባው ጊዜ አሁን ነው ሲሉ በአሶሳ ከተማ የሚኖሩ አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች አሳሰቡ፡፡

በአሶሳ ከተማ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች መካከል አቶ አሸናፊ ወልዱ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ሲመሰረት ጀምሮ ዋነኛ ዓላማው በትግራይ ህዝብ ስም ኢትዮጵያን መዝረፍ ነው፡፡

ቡድኑ በስልጣን በቆየባቸው አመታት ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የግለሰቦችን ፍላጎት ለማሟላት ይሰራ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሸባሪው ህወሓት በወረራ ገብቶ በቆየባቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች በፈጸመው ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት እታገልለታለው ሲል የኖረውን የትግራይ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር እንዲቃቃር ማድረጉን ገልጸዋል።

”አሸባሪው ህወሓት እያደረገ ያለው ጦርነት ዓላማ የሌለው ነው” ያሉት አቶ አሸናፊ የትግራይ እናቶች ዓላማ በሌለው ጦርነት የሚያልቁ ልጆቻቸውን ህይወት ለማዳን ከኢትዮጵያውያን  ጎን መቆም እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይ ተወላጆችን ከምንም ጊዜ በላይ በማቅረብ አሸባሪው ህወሓት ሀገር ለማፍረስ እየተጠቀመበት ያለውን ህዝብ የመከፋፈል ሴራው እንዲያከትም ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ከአሸባሪው ህወሓት ጀርባ  ሆነው ድጋፍ የሚያደርጉ የውጪ ሃይሎች የትግራይ ወጣትን  በከንቱ እያስጨረሱት መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ሙሉአለም አበበ የተባሉ በአሶሳ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ተገደው ወደ ጦርነት መግባታቸውን አስታውሰዋል።

አሸባሪው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት መላው ኢትዮጵያዊ በተባበረ ክንድ የሽብር ቡድኑን ለመመከት በአንድ እንዲነሳ ማድረጉን ተናግሯል።

አሸባሪው ህወሓት በወረራ በገባባቸው የአማራ እና የአፋር ክልሎች ህጻናትንና አዛውንቶችን በመድፈር፣ በመግደል፣ ንብረት በመዝረፍ ያሳየው ጭካኔ የተሞላበት የጥፋት ድርጊት ቡድኑ ለማንም ርህራሄ እንደሌለው በግልጽ እንዳሳየ ገልጸዋል፡፡

ይህም አሸባሪው ህወሓት ሀገር ለማፍረስ የያዘውን የረጅም ጊዜ እቅዱን ለማሳካት የተከተለው የመጨረሻ እርምጃ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት “ትግራይን ከኢትዮጵያ በመነጠል ሀገር እመሰርታለሁ “ የሚለውን የማይጨበጥ ህልሙን የትግራይ ህዝብ ፈጽሞ የማይቀበለው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

”ትግራይ ከኢትዮጵያ ተነጥላ ሀገር መሆን አትችልም” ያሉት አቶ ሙሉአለም፤ ይህም አሸባሪው ህወሓት  ስልጣኑን ለማስቀጠል የትግራይ ህዝብን ለማደናገር  የሚጠቀምበት ስልት መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት ባዘጋጀው የጥፋት ወጥመድ የትግራይ ክልል ሀዝብ ከወጣት እስከ አዛውንት እንደቅጠል ረግፏል ያሉት አቶ ሙሉአለም፤ “የሽብር ቡድኑ ጊዜ ሳይሰጠው ሊወገድ ይገባል ” ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።