የግራር ጃርሶ ወረዳ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

71

ፍቼ ታህሳስ 13/2ዐ14 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የግራር ጃርሶ ወረዳ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት ከ5 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ፡፡


በወረዳ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሀገርን ሉዓላዊነትን እያስከበረ ላለው ሠራዊት የሚያደርጉትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አሸብር ጌታቸው እንደገለጹት ለሁለተኛ ጊዜ ድጋፍ ያደረጉት አርሶ አደሮች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሀብቶችና ነጋዴዎች ናቸው፡፡

ከጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ባሻገር ስምንት ሰንጋ በሬዎችን፣ በሶ፣ እሽግ ውሃ በግንባር ለሰራዊቱ ለማስረከብ ኮሚቴ አዋቅረው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ አሸብር እንዳሉት ኅብረተሰቡ ባለው አቅም ከ5ዐ ብር እስከ 15ዐሺ ብር በማዋጣት ለሰራዊቱ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የቢፍቱ ሰላሌ የገበሬዎች ሕብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጄ አዱኛ እንዳሉት ዩኒዬኑ ሠራዊቱ የሀገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ያለውን አጋርነት ለማሳየት የ15ዐ ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

የመንግሥት ሰራተኛ አቶ መስፍን ሐይሌ ለሰራዊቱ የሚያደርጉት ድጋፍ ቀጣይ መሆኑን ጠቁመው ስለ ሰራዊቱ ሲያስቡ በግላቸው ያደረጉት ነገር እንደሚያንስባቸው ገልፀዋል፡፡

አሁን ካደረጉት የ3ሺ ብር የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የስንቅና ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የቶርበን አሼ ቀበሌ አርሶ አደር ዘውዴ ባልቻ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ ሕይወቱን መስዋዕት ለሚያደርገው ወታደር የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ሁሉ እንደሚያበረክቱ ገልፀዋል፡፡

ወይዘሮ ንግስት ኃይለመስቀል እንዳሉት ለሕልውና ዘመቻው ደጀኑ ሕዝብ ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመው፤ በግላቸውም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የወረዳው ጽህፈት ቤት የሕዝብ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ዓለሙ እንዳሉት ኅብረተሰቡ ለሠራዊት ያለው ፍቅርና ስሜት የላቀ መሆኑን ጠቁመው ድጋፉም የዚሁ መገለጫ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም