የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሴቶችን የፈጠራ ችሎታ በማሳደግ በኢንዱስትሪ የምርምር ማዕቀፍ ውስጥ ለማካተት እንደሚሰራ ገለጸ

4990

ሃዋሳ ሚያዝያ 23/2010 የሴቶችን የፈጠራ ችሎታ በማሳደግ በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ የምርምር ማዕቀፍ ውስጥ ለማካተት እንደሚሰራ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሴት ተማሪዎች የንግድ ስራ ፈጠራ  እቅድ ውድድር ተካሂዷል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግርና ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ዳዲ እንደገለጹት  በዩኒቨርስቲው ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የፈጠራ ስራዎች ውስጥ  ባለቤት የሆኑ ሴቶች ቢኖሩም ወደ ንግድ ስራ እቅድ የመቀየር ልምዳቸው አነስተኛ ነው፡፡

ችግሩን ለመፍታት በተነደፈ እቅድ  ሴቶችን ብቻ ያሳተፈና በነሱ የሚመራ የፈጠራ ችሎታቸውን የሚያሳዩበት የንግድ እቅድ ውድድር መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

” በዚህም ዜሮ የነበረውን የሴቶች ተሳትፎ ከ200 በላይ ማድረስ ተችሏል”  ያሉት ዶክተር ሙሉጌታ ለማጠቃለያ ውድድር የቀረቡ አምስት የንግድ እቅዶች አብዛኞቹ የሴቶችን ችግር የሚፈቱ መሆናቸው ስኬታማ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡

የንግድ እቅዶቹ ከስልጠና ጀምሮ በተገቢው አማካሪ የተከናወኑ በመሆናቸው በዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረጉ ይሆናሉ “ብለዋል፡፡

አዳዲሶቹ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችም የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስሩን በማገዝ ድርሻቸው ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰው የሴቶችን የፈጠራ ችሎታ በማሳደግ በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ የምርምር ማዕቀፍ ውስጥ ለማካተት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ሃና ላሌ በበኩሏ ቆሻሻ ሰብስቦ ማስቀመጥና ወደተፈለገው ቦታ የሚያደርስ መጥረጊያ ማሽን በማስተዋወቅ ከሁለት ጓደኖቿ ጋር ማቅረቧን ተናግራለለች፡፡

” ሀሳቡ የሃዋሳን አስፋልት የሚያጸዱ ሴቶችን በማየት የመጣ ነው” ያለችው ሃና ማሽኑ ድካማቸውን ከመቀነስ ባለፈ በአቧራና በቆሻሻ ምክንያት ሊመጡ ከሚችሉ የጤና እክሎች የሚታደጋቸው መሆኑን ገልጻለች፡፡

ፈጠራውን በከተማው ባሉ ትላልቅ ሆቴሎች በማስተዋወቅ ተቀባይነት ማግኘታቸውንና በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በሚያዘጋጀው እድል ተጠቅመው ቴክኖሎጂውን በማስተዋወቅ በአነስተኛ ዋጋ መሸጥ እንደሚፈልጉ ተናግራለች፡፡

ውድድሩ ሴቶች የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ እድል ከመፍጠር ባሻገር ልምድ የመለዋወጥ እድል የተፈጠረበት እንደሆነም ጠቅሳለች ተማሪ ሀና፡፡

አነስተኛ የመብራት ኃይል የሚጠቀምና ለመያዝ ቀላል  የሆነ ፕሮጀክተር ከጓደኞቿ ጋር መስራታቸውን የተናገረችው ደግሞ  የሶስተኛ ዓመት የኤሌክትሮ መካኒካል ተማሪዋ ቤዛዊት አለህኝ ናት፡፡

ፕሮጀክቱ የተለያዩ ፊልሞችን ለማየትና ለትምህርት አገልግሎት የሚውል እንደሆነ የገለጸችው  ተማሪ ቤዛዊት  “ቀለል ባሉ ቁሳቁሶች የሚሰራና አነስተኛ ዋጋ ስለሚኖረው  የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት ይረዳል” ብላለች፡፡

ውድድሩ ከበርካታ አዳዲስ የስራ ፈጠራዎች ጋር የተደረገና ሴት ልጆች እንዴት ወደ ገበያ መግባት እንደሚችሉ የተማሩበት እንደሆነ ጠቅሳለች፡፡

በዩኒቨርስቲው የአምስተኛ ዓመት የኢንጅነሪንግ ተማሪ ፍሬገነት ህይወት እንዳለችው በድህረ ገጽ ፣ አማካኝነት ቋሚ ደንበኞቻቸውንና ለአገልግሎት ፈላጊዎች ምግብና ሌሎች አቅርቦቶችን ማድረስ የሚያስችል ፕሮግራም ሰርተዋል፡፡

በውድድሩ አሸናፊ  ለሆኑ እቅዶች ገንዘብ የተሰጠ ሲሆን አንደኛ የሆነውን እቅድ በዩኒቨርሲቲው ስራ ለማስጀመር አስፈላጊው ግብዓት እንደሚሟላ ዩኒቨርስቲው ገልጿል፡፡