የድሬዳዋ አስተዳደርና ህዝብ በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

77

ባህር ዳር፤ ታህሳስ 13/2014 (ኢዜአ)፡ የድሬዳዋ አስተዳደርና ህዝብ በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች በጥሬ ገንዘብና በአይነት የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃርን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎችና ኡጋዞች በባህር ዳር ተገኝተው ድጋፉን ለክልሉ አስረክበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ  ድጋፉን ላደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደርና ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።

አሸባሪው ህወሓት በክልሉ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች በዜጎች ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት፣የንብረት ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል፡፡

ያጋጠመውን ችግር በመተጋገዝና በመተባበር ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት  የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሁሉን አቀፍ ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።


የተፈናቀሉ ወገኖችን በማቋቋም ወደ ቀደመው ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እንዲሁም የወደሙ የመንግስትና የግል ተቋማትን መልሶ ለመገንባት መላ ኢትዮጵያዊያን እያበረከቱ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።


የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው በአሸባሪው ህወሓት አማካኝነት በክልሉ የደረሰው ጉዳት የድሬዳዋ አስተዳደርና ህዝብ ጉዳት መሆኑን ተናግረዋል።



 በመሆኑም ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የድሬዳዋ አስተዳደርና ህዝብ በጥሬ ገንዘብ 5 ሚሊዮን እና 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብና አልባሳት ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።

በአሸባሪው ህወሓት የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የአስተዳደሩና የህዝቡ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።



የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም