የዳያስፖራው ማህበረሰብ የገና እና የጥምቀት በዓላትን በአማራ ክልል እንዲያከብር ጥሪ ቀረበ

56

ታህሳስ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የገና እና የጥምቀት በዓላትን በአማራ ክልል እንዲያከብሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጥሪ አቀረቡ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የገና እና የጥምቀት በዓላትን ለማክበር ወደክልሉ ለሚመጡ እንግዶችን ህዝቡ በኢትዮጵያዊ ባህል ተቀብሎ እንዲያስተናግድ መልዕክት አስተላልፈዋል።

"ክልሉ ብዙ ፈተናዎችን እያሳለፈ ቢሆንም በወረራ የተያዙ አካባቢዎች በመለቀቃቸው ለበአል የሚመጡ እንግዶችን ማስተናገድ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ይገኛል" ብለዋል።

"ወደ እናት አገር ቤት ሲመጣ ሁልጊዜ ደስታ ብቻ አይገኝም" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ልጅም ሃዘንንና ደስታን በጋራ የሚካፈል መሆኑን እንዳለበት ተናግረዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመጪው ታህሳስ ወር መጨረሻ የሚከበረው የገና፤ በጥር ወር የሚከበረው የጥምቀትና ሌሎች ክብረ በዓላትን ወደ ክልሉ መጥተው እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ዶክተር ይልቃል ገለጻ፤ የተደረገውን ጥሪ ተቀብለው ወደአገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን አቀባበል ለማድረግ ተገቢው ዝግጅት ተደርጓል።

አሸባሪው ቡድን በፈጸመው ወረራ ዜጎችን ከቀዬአቸው ተፈናቅሏል፣ በህዝብና በመንግስት ሃብት ላይ ውድመት መፈጸሙንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውሰዋል።

በዚህም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደአገር ቤት መጥተው የደረሰውን ጉዳት ከተመለከቱ በኋላ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ አሳስበዋል።

በአሸባሪው ቡድን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን፣ ሀብትና ንብረታቸውን የተዘረፈባቸውን ወገኖች ለመደገፍ የዳያስፖራው አስተዋጽኦ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የክልሉ ተወላጆችና መላ ኢትዮጵያዊያን ወደ ክልሉ ሲመጡ በክልሉ ብሎም በሃገሪቱ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም በልማትና ኢንቨስትመንት እድገት ላይ ምክክር እንደሚደረግም ተናግረዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም