ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ የወጡ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት መረባረብ ይገባናል

157

ደሴ፤ታህሳስ 12/2014 (ኢዜአ)፡ ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን በማጠናከር ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ የወጡ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት መረባረብ ይገባናል ሲሉ የስቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ሃይሌ አስታወቁ።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና ስራ አመራር ኢንስቲትዩት በዛሬው ዕለት ለተፈናቃይ ወገኖች፣ ለመከላከያ ሠራዊትና ለሌሎች የጸጥታ አካላት በጥሬ ገንዘብና በአይነት 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

ኮሚሽነሩ በደሴ ከተማ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በአፋርና አማራ ክልሎች በወረራቸው አካባቢዎች  ንጹሃንን በግፍ ገድሏል፣ ንብረት ዘርፏል፣ አውድሟል።

“ኢትዮጽያዊያን አንድነታችንን ጠብቀን ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ የወጡ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት ልንረባረብ ይገባል ” ሲሉ አስገንዝበዋል።

”ወቅቱ አንዳችን ለአንዳችን የምንተጋገዝበት፣ የምንረዳዳበትና የውጭ ጫናውንም በጋራ የምንከላከልበት ወሳኝ ወቅት ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ኪሚሽኑ የሚችለውን ሁሉ በማድረግ የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 2  ሚሊየን ብር በጥሬ በቼክ የተደረገና ቀሪው 900 ሺህ ብር ግምት ያለው በሶና ቆሎ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ ጨምሮ የህፃናት ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስና  ና ሌሎች አልባሳትን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የስራ አመራር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ውብአምላክ እሸቱ በበኩላቸው “በሽብር ቡድኑ የወደሙ መሰረተ ልማቶችንና ተቋማትን ስራ ለማስጀመር የድርሻችን እንወጣለን” ብለዋል።

አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሳይ ማሩ በበኩላቸው “አሸባሪው ህወሓት  በወረራ ይዞ በቆየባቸው 25 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ንጹሀንን በግፍ ገድሏል ንብረት ላይ ውድመት አድርሷል” ሲሉ ተናግረዋል።

የወደሙትን መልሶ ለማቋቋምና ለተቸገሩ ወገኖች  በእለት ምግብ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሁሉም ቦታ መድረስ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።

 “መንግስታዊና መንግስታዊ  ያልሆኑ ድርጅቶች እና ህብረተሰቡ ያላቸውን በማካፈል ይህን ክፉ ቀን በጋራ ለማለፍ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል ።