ለተፈናቃይ ወገኖች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ ተደረገ

176

ደብረ ብርሃን ታህሳስ 12/2014 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅትና የዲላ ዩኒቨርስቲ ሰራተኞች በአሸባሪው ህወሀት ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ፣ አልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስትክስ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ምህረት አብ ተክሉ በደብረ ብርሃን ከተማ ተገኝተው ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት የድርጅቱ ሰራተኞች ከዚህ በፊት ለህልውና ዘመቻው የወር ደመወዛቸውን ለግሰዋል።

ሰራተኞቹ ንጹሃን ዜጎች በአሸባሪ ሃይሎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ከደረሰባቸው ችግር በላይ አሳዛኝ ድርጊት የለም በሚል  አጋርነታቸውን ለመግለጽ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ድጋፉየዳቦ ዱቄት፣ ማካሮኒ፣የህፃናት አልሚ ምግብን ጨምሮ አልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ  ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት  የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት ሁሉ ሰራተኞቹ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውንም አስታውቀዋል ።

የባህርተኞች ተወካይ ኤቢ ግዛው እምሩ በበኩላቸው “ኢትዮጵያን ለማዳን የሁሉም ያልተቋረጠ ርብርብ ያስፈልጋል” ብለዋል።

“አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ አገር ለማፍረስ የሚያካሂዱትን እኩይ ሴራ በየደረስንበት ሁሉ ለዓለም ህዝብ በማሳወቅና በማስገንዘብ  ኢትዮጵያ ወደ ቀደመው ገናና ክብሯ እንድትመለስ እንሰራለን” ሲሉም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የዲላ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ለተፈናቃይ ወገኖች 765 ሺህ ብር ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ አበርክቷል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ  ድጋፉ የጤፍ ዱቄት፣ብርድ ልብስ፣ካርቶን የሴቶች ንጽህና መጠበቂያና ሌሎች ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል።

“የሃገሪቱን ሰላም በመመለስ በሃብትና በስነ ልቦና የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመደገፍ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል” ብለዋል።

 ”የተደረገው ድጋፍ የወገን አለኝታነትን ከማረጋገጡም በላይ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ከፍተኛ ፋይዳ አለው” ያሉት ደግሞ ድጋፉን የተረከቡት የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ጌታቸው በለጠ ናቸው።

“ድጋፉ ለተፈናቃዮች በፍጥነት እንዲደርስ ይደረጋል “ያሉት ተወካዩ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረትም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።