የወልዲያ ደጋግ እናቶች ህይወታችንን ታድገውታል

571

አገር በእናት ሲመሰል፤ የአገር ፍቅርም በእናት ፍቅር ሲወከል እውነትነት አለው። የአገር ልጆች ለእናት አገራቸው ይደማሉ፤ ይቆስላሉ፤ በመስዕዋትነታቸውም አገራቸውን ያጸናሉ።

የእናት እና የአገርን ተመሳስሎሽ ደግሞ በወይዘሮ ታክላ ምህረቴ እና ወይዘሮ አባይነሽ ይማም ሰብዓዊ ድርጊት ይገለጣል።

አሸባሪው የሕወሃት ቡድን ወልድያን እና አካባቢውን በወረራ ይዞ በቆየባቸው ጊዜያት በሰው ልጆች ላይ ይፈጸማሉ ተብሎ የማይገመቱ መልከ ብዙ ግፍና ሰቆቃዎችን ሲፈጽም ቆይቷል።

ንጹሃንን ያለምክንያት በማንነታቸው ብቻ በጅምላ የሚጨፈጭፍ ቡድን ለአገራቸው ዘብ የቆሙ ወታደሮችን የደበቁ እናቶች ቢያገኝ ምን ያህል ጭካኔ ሊያሳርፍ እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

እናም በፓርቲ አባልነትና በመንግስት ደጋፊነት ጥርጣሬ ሺዎችን የረሸነ ቡድን አካባቢያቸውን ሲቆጣጠር የወልድያ እናቶች “ልጆቼ” የሚሏቸውን ቁስለኛ ወታደሮችን ከጓዳቸው ደብቀው ነፍሳቸውን አተረፉ።

ወይዘሮ አባይነሽ እና ወይዘሮ ታክላን መሰል እናቶች የአገር ፍቅርን፣ የሰብዓዊነትን ጥግ እና ሞራል ልዕልና በተግባር ያሳዩ ኢትዮጵያዊ እሴትን ያረጋገጡ እናቶች ናቸው።

ሁለቱ እናቶች በውጊያ ላይ የቆሰሉ ወታደሮችን በጨፍጫፊውን ቡድን ስጋት ሳይበገሩ ለኢትዮጵያ ህልውና የሚዋደቅ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ከቤታቸው አስጠግተው ተንከባክበው፤ ከቁስላችው አክመው ህይወታቸውን ታድገዋል።

ወልድያ ነጻ ከወጣ በኋላ ከቤታቸው በራፍ ከሚገኝ የማንጎና ቡና ተክል ስር ተጠልለው ሕይወቱን ከታደጉት ላይ ወታደር ጋር በደስታ እየተሳሳቁ ያገኘናቸው እናት ወይዘሮ ታክላ ድርጊቱን ያስታውሳሉ።

ሁሉም ደጃፉን ዘጋግቶ በተቀመጠበት ቅጽበት በእሳቸው አጥር ላይ መለዮ የለበሰ ቁስለኛ ወታደር ሲመለከቱ ክፉኛ ማዘናቸውን እና ወደቤታቸው አስገብተው ማቆየታቸውን ይናገራሉ።

የወታደሩን ሕይወት ለመታደግ ጎረቤቶቻቸው ርዳታ እንዳልተለያቸው ገልፀው፤ ትናንት የተጨነቁለት እንደ ልጅ ተንከባክበው ከቁስሉ እንዲያገግም ያደረጉትን ወታደር ድኖ በማየታቸው አምላካቸውን ያመሰግናሉ።

እነዚህ ሀገር ጠባቂ ወታደሮች ችግር በገጠማቸው ጊዜ የተንከባከብኳቸው እንደልጆቼ ስለማያቸው ነው ብለዋል።

በእነዚህ ደፋርና ደጋግ እናቶች እንክብካቤ ሕይወታቸው የተረፉ የሰራዊቱ አባላትም ይናገራሉ።

በወይዘሮ ታክላ ሕይወቱን የታደጉለት ወታደር ተመስገን ካርታ “በቁስላችን ሳይሸማቀቁ እንደልጅ ተንከባክበው  አዳኑን” ብሏል።

ወታደር ተመስገን በውጊያ ቆስሎ በተጠጋበት ቤት ደጃፍ ላይ የማያውቃቸው እናት ስቅስቅ ብለው አልቅሰው “ናልኝ ልጄ በማለት ተቀበሉኝ፤ ልብሴንም ቀየሩልኝ” ይላል።

በውጊያው ቆስሎ ለ24 ሰዓት ህክምና ሳያገኝ መቆየቱን የሚናገረው ተመስገን፤ የህመሙን ስቃይ ካልወለዱት እናቱ እንክብካቤ ታክሞ መዳኑን ይናገራሉ።

ወይዘሮ ታክላ ምንም ሰላውቃት፤ ሳታውቀኝ በኢትዮጵዊነት መንፈስ በባህላዊ መንገድ በማከም እና ሽንት ቤት በማመለለስ ህይወቴን ታድጋኛለች ይላል።

በተመሳሳይ ሌላዋ የወልዲያ ነዋሪ ወይዘሮ አባይነሽም ሰውን እንደራስ ማየት ሰዋዊ ባህሪ ነው፣ ግዴታም ነው ይላሉ።

“በእግዚአብሄር ቃል የተቸገረን መንከባከብ፣ የተራበን ማብላት ስለሆነ ብቸገርም እንኳን ቆሎ ቆርጥሜም ቢሆን እንግዳዬ ጋር የሚሆነውን እቀበላሉ በሚል ከቤቴ ማቆየት ፈለግሁ” ይላሉ።

“ኢትዮጵያን ለማዳን፤ እኛን ሕይወት ለማዳን ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የመጣን መከላከያ ሰራዊት አባል ቤት ለእንግዳ ብዬ መንከባከብ ግዴታዬ ነው፤ ለወለዱ እናቶች ሁሉም ልጅ ልጅ ነው” ይላሉ እናቶች።

ወይዘሮ አባይነሽ ያስጠጉት ወታደር ወልዴ ሙላው “እንደእናት ደረሱልኝ፣ ከአካባቢው ሰዎች ጋር ተንከባክበውም ለዚች ቀን አበቁኝ” ብሏል።

ባልጠበቅሁት መልኩ ወይዘሮ አባይነሽ ወላጅ እናት ሆነው “ተንከባክበው ሕይወት ሰጥተውኛል፤ አመሰግናለሁ” ይላል።

የወልዲያ ከተማ እናቶች እናቶች ባሳዩት የመልካምነት ጥግ ብዙሃኑን የደስታ እምባ አራጭተዋል፤ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ የአገር ሉዓላዊነትና ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የወጣን ወታደር መጠበቅና መንከባከብ ይገባናል ብለዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።