አሸባሪው ህወሃት የፈጸማቸው የወንጀል ድርጊቶችን የሚያጣሩ 11 መርማሪ ቡድኖች ተሰማርተዋል

87

ታህሳስ፤ 12/2014(ኢዜአ) በአማራና አፋር ክልሎች አሸባሪው የህወሃት ቡድን የፈጸማቸው የወንጀል ድርጊቶችን የሚያጣሩ 11 መርማሪ ቡድኖች መሰማራታቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ አባል የሆነው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌዴራል ፖሊስ   ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራልና የወንጀል ምርመራ ቢሮ  ኃላፊ ዘላለም መንግሥቴ እንደገለጹት፤ አሸባሪ ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች የፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በወንጀል የሚያስጠይቁት ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ሰጪነት የወገን ሃይል  ወንጀል ፈጻሚውን አሸባሪ ቡድን  መመከት መቻሉን ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት በገባባቸው ክልሎች የፈጸማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማጋለጥ እንቅስቃሴ መጀመሩን ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም አስረድተዋል።

ቢሮው ከፍትህ ሚኒስቴርና ከክልሎቹ ፖሊስ ጋር የተቀናጀ ኮማንድ በማደራጀትና የሥራ መመሪያ በመስጠት ማሰማራቱን አስታውቀዋል።

ቡድኖቹ በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም በአፋር በጭፍራና ካሳጊታ መግባታቸውን አስረድተዋል።

በአሸባሪው ህወሓት የተገደሉ፣ የተደፈሩ፣ የተጨፈጨፉና ግፍ የተፈጸመባቸው ንጹሃን ዜጎች ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር እንዲጠየቅ ይደረጋል ብለዋል።

የምርመራ ቡድኑ የደረሰበት ውጤትም በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ሌሎች የአለም አቀፍ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለዓለም ህዝብ ይፋ እንደሚሆን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በበኩላቸው፤ ጦርነቱ በታሪክ ተሸንፈው የማያውቁት ኢትዮጵያዊያን ሀገርን ለማፍረስ ከተነሱ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው ጋር  እንደሆነ አስረድተዋል።

በዚህም የወገን ሃይል በህዝብ ላይ ሰቆቃ የፈጸመውን የህውሃት አሸባሪ ቡድን መመከቱን ጠቅሰው፤ ቡድኑ በወረራ በያዛቸው የክልሉ አካባቢዎች ንጹሃንን በመግደልና በማፈናቀል የሥነ ልቡና ጉዳት ከማድረሱም ባለፈ  ሃብትና ንብረታቸውን በመዝረፍና በማውደም በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁን ወንጀል መፈጸሙን ተናግረዋል።

የፌዴራል ፖሊስም ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር አሸባሪው የህወሃት ቡድን በህዝብ ላይ የተፈጸመውን ወንጀል በመመርመርና በማጣራት በዓለም የፍትህ አደባባይ ማቅረብ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በዚህም በንጹሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ወንጀል የፈጸሙ አካላት ዳግም ለወንጀል እንዳይነሳሱና እንዳያስቡ የሚያደርግ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሀት በአማራና በአፋር ክልሎች በመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች ፀጥታ ሃይሎች ተሸንፎ በመፈርጠጥ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም