ሁሉም ዜጋ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት ስራዎች ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል

85

ታህሳስ 12/2014 (ኢዜአ) ሁሉም ዜጋ በህብረ-ብሄራዊ የትብብር መንፈስ በመነሳት በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት ስራዎች የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉ የሃረሪ ክልል ርእሰ-መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስገነዘቡ።

የሃረሪ ክልል በአሸባሪው ህወሀት ወራሪ ሀይል  በአፋር ክልል  የወደሙ የጤና ተቋማትን ስራ ለማስጀመር  7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አበርክቷል።

ክልሉ በተጨማሪም በአፋር ክልል በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖችድጋፍ የሚውል በጥሬ ገንዘብ  3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ  አድርጓል።

በሀረሪ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ የተመራ ልኡክ ዛሬ ሰመራ ከተማ በመገኘት ድጋፉን ለአፋር ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ አስረክቧል ።


በርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ የሃረሪ ክልል ርእሰ-መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት የአፋር ህዝብ ከመከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን የህወሃት የሽብር ቡድን በሀገር ላይ ደቅኖት የነበረውን የህልውና አደጋ በመቀልበስ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በማስከበር አኩሪ ታሪክ ፈጽሟል።

የሽብር ቡድኑ በወረራቸው የአፋርና አማራ አካባቢዎች ዜጎችን በግፍ በመግደልና ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የተገነቡ መሠረተ-ልማቶችን በማውደም የህዝብ ጠላትነቱን ማሳየቱን ተናግረዋል።

በአሸባሪው ወራሪ ሀይል የወደሙ መሠረተ-ልማቶችን ወደ ቀደመ ይዞታቸው በፍጥነት መልሶ ዜጎች ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ የማስቻል ተግባር በመንግስት ብቻ የሚከወን አለመሆኑን ጠቁመዋል ።

ሁሉም ዜጋ በህብረ-ብሄራዊ የአብሮነትና ትብብር መንፈስ  በመነሳት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት ስራዎችየበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል ።

የሀረሪ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ በአፋር ክልል በአሸባሪው የወደሙ ጤና ተቋማትን  ወደ ስራ ለማስገባት በሚደረገው ጥረት የድርሻውን ለማበርከት ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

በአሸባሪው ቡድን ለተፈናቀሉና  ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ችግር ለማቃለል በጥሬ ገንዘብ የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።

የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለማጥፍት ከ50 አመት በላይ በድብቅ ሲዘጋጅ የኖረ የጥፋት ሀይል መሆኑን ተናግረዋል።
 
"አሸባሪው አላማውን ለማሳካት በመንግስትና ግለሰብ ይዞታዎችና ንብረቶች ሳይወሰን የእምነት ተቋማትን ጭምር በማውደም ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪም ጋር ጭምር ጦርነት ከፍቷል" ሲሉ የህወሀትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊትና የጭካኔ ዝግ ገልጸውታል ።


አሸባሪው ቡድን በእብሪት ተነሳስቶ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመው የግፍ ጽዋ ሞሎቶ መጥፊያው መቃረቡን ያረጋገጠ ክስተት መሆኑን ጠቁመው በዚህ ሂደት ሁለም ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ለመታደግ እያሳየ ያለው ንቁ ተሳትፎና የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍ ተግባር የሚያኮራ መሆኑን አመልክተዋል።

የሃረሪ ክልላዊ መንግስት ያደረገው ድጋፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ህብረተሰብ ክፍሎች የተሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ለማጎልበት አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው፤ለተደረገው ድጋፍ በክልሉ መንግስትና ህዝብ እንዲሁም በተጎጂዎች ስም ምስጋና አቅርበዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም