ከስድስት ወር ልጇ ለይተው ገደሏት፤ ይኸው እኔም ህጻኑን ታቅፌ በሀዘን እርር ብያለሁ

81

ታህሳስ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ከስድስት ወር ልጇ ለይተው ገደሏት፤ ይኸው እኔም ህጻኑን ታቅፌ በሀዘን እርር ብያለሁ" ሲሉ የሟች እናት ወይዘሮ አድና መኮንን የመረረ ሀዘናቸውን ይገልጻሉ።

አሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል በአማራና በአፋር ክልሎች በወረራ ይዟቸው በነበሩ አከባቢዎች የፈጸመው ግፍ የብዙዎችን ህይወት ሲቀጥፍ ለቀሪዎች ደግሞ ሀዘንና ጸጸት ሆኗል።

ቡድኑ ንጹሃንን ጨፍጭፏል፤ ሴቶችን ደፍሯል፤ ንብረት ዘርፏል መውሰድ ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል፡፡

የሽብር ቡድኑ የጭካኔ እጆች ካረፉባቸው ከተሞች መካከል ደግሞ የሰሜን ወሎ ዞኗ መርሳ አንዷ ናት፡፡

አሸባሪ ቡድን በከተማዋ በቆየባቸው ጊዜያት በቃላት የማይነገሩ ግፎችን የፈጸመ ሲሆን፤ የስድስት ወር ህጻን ለታቀፈች እናት እንኳ የሚራራ ማንነት የለውም፡፡

የሽብር ቡድኑ ወራሪ ኃይሎች በመርሳ ከተማ የስድስት ወር ህፃን እናትና ወንድሟን "ያላችሁን ብር ደብቃችኋል፤ ብሩን ካላመጣችሁ" በሚል ሰበብ በግፍ ገድለዋቸዋል፡፡

የሟቾቹ እናት ወይዘሮ አድና መኮንን በሽብር ቡድኑ ሁለት ልጆቻቸው ተገድለው የሰቆቃ ጊዜ እያሳለፉ መሆኑን ይገልፃሉ፤ ሀዘናቸውም ከፊታቸው ይነበባል፡፡

"ከስድስት ወር ልጇ ለይተው ገደሏት፤ ይኸው እኔም ህጻኑን ታቅፌ በሀዘን እርር ብያለሁ" ሲሉም ነው አሸባሪ ቡድኑ በቤታቸው ያደረሰውን መከራ የገለጹት፡፡

ሌላኛው ሟች ልጃቸውም የቤተሰቡ ተስፋ የሆነ የ15 ዓመት ታዳጊ ነበር።

አሸባሪው የታዳጊው ህልም የቤተሰቡን ተስፋ ነጥቋል።የሟቾቹ አባት አቶ ሽፈራው ወርቁ በበኩላቸው "ህፃን ልጅ እያለቀሰ እናቱን ለይተው የሚገድሉ ጨካኞች" ሲሉ የሽብር ቡድኑ በቤተሰባቸው ላይ የፈጸመውን ግፍ ይገልጻሉ፡፡

የህጻኑን እናት ከትንሽ ወንድሟ ጋር ከቤታቸው አውጥተው በራቸው ላይ ገድለዋቸው መሄዳቸውን የሚገልጹት አባት፤ በዘመኔ እንደዚህ አይነት ጭካኔና ግፍ አይቼ አላውቅም ሲሉ ይናገራል፡፡

ንጹሃንን በግፍ መግደል፣ ሴቶችን መድፈር፣ ገንዘብ መቀማት፣ መደብደብ፣ ማሰርና ማንገላታት የሽብር ቡድኑ መለያ ባህሪ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ የሟቾቹ ጎረቤት አቶ ተፈራ አይተነዋል ናቸው፡፡

"በህይወቴ እንደዚህ አይነት የግፈኞች ስብስብ አይቼ አላውቅም " የሚሉት አቶ ተፈራ፤ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች መርሳ ከተማ ከገቡበት ቀን ጀምሮ ነዋሪዎቹ የሰቆቃ ህይወት ሲገፉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም