በተሽከርካሪ አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በተሽከርካሪ አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት አለፈ

ሻሸመኔ/ጎባ፤ ታኅሳሰ 12/2014(ኢዜአ ) በምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ እና በባሌ ዞን ጎባ ወረዳዎች በደረሰው የተሽከርካሪ አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
በምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥር ዲቪዥን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጎሴ ዴኮ እንደገለጹት፤ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 - 35772 ኦሮ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ከዶዶላ ወረዳ ድንች ጭኖ ወደ ሻሸመኔ በመጓዝ ላይ እያለ ለገ ቢሊቃ በተባለው ልዩ ቦታ ተገልብጦ ከላዩ ላይ ተጭነው ሲጓዙ የነበሩ የአምስት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ አልፏል።
አሽከርካሪውና ረዳቱ ቢተርፉም በደረሰባቸው ከባድ አደጋ በዶዶላ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ የተሽከርካሪ አደጋ በተደጋጋሚ እየተከሰተ መሆኑን ያወሱት ኢንስፔክተር ጎሴ፤ አሽከርካሪዎች ተገቢ ባልሆነ መልኩ ሰዎችን ከማሳፈር መቆጠብና ሰዉም ለራሱ ሕይወት ሲል ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በተመሳሳይ ዜና በባሌ ዞን ጎባ ወረዳ ልዩ ስሙ ሲንጃ በተባለ አካባቢ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 43678 ኦሮ ሚኒባስ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ዛሬ ረፋድ አምስት ሰዓት ላይ መንገዱን ስቶ በመገልበጡ የአራት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ማለፉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ተወካይ ኮማንደር ናስር ኡመር ገልጸዋል።
.jpg)
በአደጋው ከባድና ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው 13 ሰዎች በጎባ ሪፌራል ሆስፒታል ህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ያመለከቱት።
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑ ተመልክቷል።