በጡረታ ከማገኘው ቆጥቤ ለተፈናቀሉ ወገኖች 30ሺህ ብር ለግሺያለሁ

166

ሰመራ፤ ታህሳስ 12/2014(ኢዜአ)የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት በጡረታ ከማገኘው ቆጥቤ ካስቀመጥኩት ወስጥ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል ላፈናቀላቸው ወገኖች ድጋፍ እንዲውል 30ሺህ ብር ለግሺያለሁ ይላሉ አቶ ብርሃኑ ታቶ ።

ዕድሜያቸው 75 ዓመት እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ ታቶ  የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ  ናቸው።

ገንዘቡን የለገሱት ዛሬ በሰመራ ከተማ በመገኘት  ለተፈናቃይ ወገኖች እንዲደርሳቸው  በክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ  በኩል ነው።

ከመምህርነት ጀምረው በተለያዩ የእርከን ደረጃ  በመንግስት ስራ ቆይተው  ጡረታ ከወጡ በኋላ  በሚያገኟት ውስን ገቢ በቢሾፍቱ ከተማ ኑሯቸውን እየመሩ ነው።

አያታቸው በአድዋ ጦርነት አባታቸውም እንዲሁ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት የሀገራቸውን ሉአላዊነት ለማስከበር ሲታገሉ  በክብር እንደተሰዉ በማስታወስ በሀገር ፍቅርና ወዳድ ቤተሰብ ውስጥ በፍጹም ኢትዮጵያዊነት ወግና ባህል ተቀርጸው  ማደጋቸውን ነው  አቶ ብርሃኑ ለኢዜአ የተናገሩት።

ከዚህም የተነሳ እሳቸውና ሌሎች አራት ወንድሞቻቸው በሀገራቸው ጉዳይ ከማንም ጋር እንማይደራደሩ ኩሩ ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ ነው የሚገልጹት።

በእያንዳንዱ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ልክ እንደቤተሰባቸው  ጉዳይ  በየዕለቱ የሚያስጨንቃቸውና የሚወያዩበት መሆኑን ይናገራሉ።ምክንያቱንም ሲገልጹ ወጦቶ መግባትና ሃብት ማፍራት ብሎም  ልጅ ወልዶ መሳምና ማሳደግ አልፎም ለወግ-ማዕረግ መብቃት  የሚቻለው ሀገር ታፍራና ተከብራ በሰላም ስትኖር ነው።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በሀገር ላይ  የደቀነብንን  አደጋ ለመቀልበስ በዕድሜያቸው መግፍት ምክንያት ግንባር ሄደው መታገል ባይችሉም ከሰራዊቱና ከተጎዱ ወገኖች ጎን በመቆም የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አቶ ብርሃኑ ያስረዳሉ።

በሚኖርቡት ቢሾፍቱ ከተማ ሰርጎ ገብ የጥፋት ተላላኪዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን አካባቢቸውን እየጠበቁ መሆኑን  ነው የተናገሩት ።


ዛሬ ያደረጉት ድጋፍ ሃብትና ንብረት ተርፏቸው ሳይሆን ለሀገር ሰላምና ደህንነት መቆም የዜግነት ግዴታቸው እንደሆነ በማመን 30ሺህ  ብር መለገሳቸውን ነው አቶ ብርሃኑ ያስታወቁት።

ድጋፉ ስለሀገር ክብር ሲል ውድ ዋጋ ለከፈለው ለአፋር ወገናቸው ያላቸውን ክብርና ወገናዊ አጋርነታቸውን ለመግለጽም ጭምር እንደሆነ ነው የተናገሩት።

አሁን የገጠመን ሀገራዊ ፈተና አሸባሪው ቡድን በስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት በትወልዱ ላይ የተሰራው እኩይ ሴራ ውጤት ነው።
 
አቶ ብርሃኑ በትዳር ህይወታቸው ያፈሯቸውን አራት ልጆች በጨዋ ኢትዮጵያው ወግና ባህል ቀርጸው በማሳደግ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን መወጣታቸውን አብራርተዋል።


ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚሁ አግባብ ልጆቹን  በሀገር ፍቅርና  ወዳድነት መንፈስ ከመቅረጽ በተጨማሪ ከሰራዊቱና ከተጎጂ ወገኖች ጎን እንዲቆም ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው ፤ የአቶ ብርሃኑ ታቶ የገንዘብ ድጋፍ ሀገር ወዳድነትን በተግባር ያሳየና አስተማሪነቱ ከፍ ያለ  መሆኑን ነው የገለጹት።

አቶ ብርሃኑ ረጅም ርቀት አቋርጠው የአፋር ወገናቸው መፈናቀልና ለችግር መጋለጥ አሳስቧቸው  ድጋፍ ለማድረግ በመምጣታቸው በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም ምስጋቸውን አቅርበዋል

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም ባለሃብቱና ዲያስፓራው የአቶ ብርሃኑ አርአያነት በመከተል ሀገር ለማፍረስ  በተነሳው አሸባሪው የህወሃት ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በማካፈልና በመደገፍ  የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።