የኮቪድ ወረርሺኝ ተጽዕኖ እንዲቋቋሙ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14 ሺህ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ድጋፍ ተደርጓል

68

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 12/2014(ኢዜአ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባለፉት ስምንት ወራት የኮሮና ወረርሺኝ ተጽዕኖ እንዲቋቋሙ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14 ሺህ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ድጋፍ አደረገ ።

በሚኒስቴሩ የቢዝነስ ኢመርጀንሲ ቡድን መሪ አቶ አብርሃም ናትናኤል ለኢዜአ እንዳሉት ሚኒስቴሩ ኢንተርፕራይዞች በኮቪድ ተጎድተው ከሥራ እንዳይወጡ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።

ሚኒስቴሩ ለኢ-መደበኛና መደበኛ ኢንተርፕራይዞች የደሞዝና የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ለመደበኛ ኢንተርፕራይዞች በአነስተኛ ወለድ ብድር ማመቻቸቱን ተናግረዋል።

የደሞዝ ድጋፉ ኢንተርፕራይዞቹ ሰራተኞቻቸውን በሥራ ላይ እንዲያቆዩ ለማድረግና በኢ-መደበኛ ንግድ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችም ከሥራ ውጪ እንዳይሆኑ የተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ስምንት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ14 ሺህ በላይ መደበኛና ኢ-መደበኛ ኢንተርፕራይዞች የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም 45 ሺህ ሰዎች ከስራ ውጪ እንዳይሆኑ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪ ለ1 ሺህ 280 ኢንተርፕራይዞች በአነስተኛ ወለድ ብድር እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

እስካሁን 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በድጋፍና ብድር መልክ ለኢንተርፕራይዞች መሰጠቱን ገልጸዋል።

ከዚህም ውስጥ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርኃ ግብር /ዩ ኤን ዲ ፒ/ የተሸፈነ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ድጋፉን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም