ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ እያሳዩት ያለው አንድነት ኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ፈተና እንድታሸንፍ የሚያደርግ ነው

209

ታህሳስ 12/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ እያሳዩት ያለው አንድነት ኢትዮጵያ  የትኛውንም አይነት ፈተና እንድታሸንፍ የሚያደርግ ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን  አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው ከበደ ዴሲሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በውጭ ሀገራትና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት ለሀገራቸው ህልውና እየታገሉ ነው፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተቃጣውን አደጋ በድል እየመከቱት ይገኛሉ ያሉት አቶ ከበደ፥ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውንና መንግስትን በማገዝ ረገድ አዲስ ታሪክ እየጻፉ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት በዜጎች መካከል መከፋፈልን ለመፍጠር የተለያዩ ሴራዎችን ሲፈፅም መቆየቱን አስታውሰው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን በማጠናከር ሀገራቸውን አስቀድመው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

”ብዙ ሀገራት በውጭ ጣልቃ ገብነት ፈርሰው አይተናል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በኢትዮጵያም በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ጣልቃ ገብነት ፍላጎቶች መስተዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ፍላጎቶች ሊሳኩ ያልቻሉት ደግሞ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ጠብቀው ለሀገራቸው ህልውና በጋራ በመቆማቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ እያሳዩት ያለው አንድነት ኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ፈተና እንድታሸንፍ የሚያደርግ  ስለመሆኑም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው የውጭ ሀገራት ጫና እና ጣልቃ ገብነት የአፍሪካ መሪዎችን እጅ በመጠምዘዝ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን ለመጫን የሚደረግ ሴራ አካል መሆኑንም ገልጸዋል።

አፍሪካውያን ይህን ተገንዝበው ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውን አንስተው፤ ይህም ኢትዮጵያ ዛሬም የነጻነት አርማና ተምሳሌት ሀገር መሆኗን ያሳየ ነው ብለዋል።

አፍሪካውያን በ “#NO MORE”  “#በቃ” ንቅናቄን በስፋት በመቀላቀል የውጭ ጣልቃ ገብነት በቃ በሚል ከፍ ያለ ድምጽ እያሰሙ ስለመሆኑ ገልጸዋል።