በአማራ ክልል አንድ ሚሊዮን ወደ ሀገር ቤት ጥሪን ባማከለ መልኩ የገናና የጥምቀት በዓላትን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

50

ባህርዳር ታህሳስ 12/2014(ኢዜአ) በአማራ ክልል ''ገናን በላልይበላ ፤ ጥምቀትን በጎንደር'' በደመቀ ሁኔታ ለማክበር አንድ ሚሊዮን ወደ ሀገር ቤት ጥሪን ባማከለ መልኩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በዓላቱን በላልይበላ እና በጎንደር በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው።

በክልሉ በርካታ የቱሪስት መስህብ ሀብቶች ቢኖሩም በኮሮና ቫይረስ ክስተት እንዲሁም በህወሓት የሽብር ቡድን ወራራ ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴው መቀዛቀዙን ገልጸው በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ሲባል የገናን በዓል በላልይበላ፤ ጥምቀትን ደግሞ በጎንደር በተለየ ድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአላቱን ለማክበር አንድ አብይ ኮሚቴና በየደረጃው ንኡሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ለቱሪስቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

"በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አንድ ሚሊዮን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የገና በዓልን በአገራቸው እንዲያከብሩ ጥሪ መደረጉን ተከትሎ ወደ አገር ቤት የሚመጡ ዜጎችን ታሳቢ በማድረግ ዝግጅቱ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት"።

"አሸባሪው ህወሓት በታሪካዊቷ የላልይበላ ከተማ በወራራ በቆየባቸው ጊዜያት የቱሪስት ማረፊያ ሆቴሎችን ጨምሮ የቴሌኮሚኒኬሽን፣ የኤሌክትሪክና የውሃ መስመሮችን ሳይቀር አውድሟል" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመጠገን የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ያመለከቱት ሃላፊው "የዝግጅት ሥራው ከውጭ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን እንዲሁም የአገር ውስጥ ጎብኚዎች በዓሉን እንደቀደመው በደመቀ ሁኔታ እንዲያከብሩ የሚያስችል ነውም" ሲሉ ገልጸዋል።

"ቱሪስቱ ምንም ነገር ሳይጓደልበት ከአሁን በፊት በለመደውና ባየው መልኩ በሁሉም ነገር ተመችቶት እንዲጎበኝ ይደረጋል" ብለዋል።

አቶ ኤርሚያስ አንዳሉት የሆቴል ባለንብረቶችና አስጎብኚዎች ለቱሪስቶች ምቹና የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በክልሉ በታህሳስ፣ ጥር እና የካቲት ወራት በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት እንደሚከበሩ ጠቅሰው፤ የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የሚያግዙ ተግባራትም እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም