በትራንስፖርት ላይ የሚታየው የጥንቃቄ ጉድለትና የቁጥጥር መላላት ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ መጨመር አንድ ምክንያት ሆኗል

159

አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2014(ኢዜአ) በትራንስፖርት ላይ የሚታየው የጥንቃቄ ጉድለትና የቁጥጥር መላላት ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ መጨመር አንድ ምክንያት ሆኗል።

በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሚያዙ ሰዎች አብዛኞቹ በምርመራ አለመታወቃቸውንና በአህጉሪቱ ውስጥ በበሽታው ከተያዙ ሰባት ሰዎች መካከል ስድስቱ ተመርምረው ያልተለዩ መሆናቸውን የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

አሁን ላይ በአፍሪካ በኮቪድ-19 መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 9 ሚሊዮን ቢሆንም የዓለም ጤና ድርጅት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር 59 ሚሊዮን ነው ይላል።

በዚህም አፍሪካ በአራተኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተመታች እንደምትገኝ የአለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ተጠሪ ዶክተር ማቲሲዲስ ሞቲ ትላንት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

አፍሪካ ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ በአዲሱ የኮቪድ 19 ዝርያ ኦሚክሮን የተያዙ ዜጎቿ ቁጥር በ83 በመቶ መጨመሩን ተጠሪዋ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮና ቱኒዚያ ደግሞ ከፍተኛውን የታማሚዎች ቁጥር አስመዝግበዋል፡፡

የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል ቀደም ሲል ጥብቅ የመከላከያ መንገዶች ሲተገበሩ ቢቆይም አሁን ላይ ግን መዘናጋቱ በስፋት እየታየ ነው፡፡

በተለይም በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ከዚህ ቀደም ሲደረግ የነበረው ማስክ አድርጎ መሳፈርና የተሳፋሪ ቁጥርን መጠን በእጅጉ ተዘንግቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ባለሥልጣን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ይርጋለም ብርሃኔ፤ከዚህ ቀደም የወጣው መመሪያ በአሁኑ ሰዓት በሚገባ እየተተገበረ እንዳልሆነና የሚደረገው ቁጥጥር መላላቱንም ገልጸዋል።   

ህብረተሰቡን ማስተማርና ተሽከርካሪዎችን ኬሚካል መርጨቱ ቢቀጥልም፤ በአቅም ውስንነትና በመዘናጋት የመመሪያው አተገባበር ላይ ክፍተት እየተስተዋለ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የህብረተሰቡ መዘናጋት በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ቦታዎች እየተስተዋለ መሆኑን ጠቅሰው የጥንቃቄና የመከላከል ሥራው እንዲጠናከር የሚመለከታቸው አካላት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ እስከ ትላንት ድረስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 377 ሺህ ሲሆን በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 6 ሺ 872 ነው፡፡