የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ 12 ጊዜ ስብሰባ መቀመጡ ለምን?

198

ታህሳስ 12/2014/ኢዜአ/ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ 12 ጊዜ ስብሰባ መቀመጡ ለምን?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ሥልጣን ያለው አካል ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት 15 አባል አገራት ያሉት ሲሆን ከእነዚህ አገራት መካከል

አምስቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ቋሚ አባል አገራት ናቸው።

አስሩ ደግሞ በየዓመቱ የሚቀያየሩ እና ድምጽን በድምጽ የመሻር አቅም የሌላቸው አባል አገራት ናቸው።

ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ቻይና ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ በዓለም ላይ ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ሚናውን መወጣት ነው።

ከ190 በላይ አባል አገራትን ያቀፈው ድርጅቱ ከተመሰረተ ከ70 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ግን የተወሰኑ ኃያላን አገራትን የፖለቲካ ፍላጎት ከማስጠበቅ ባለፈ ተራምዶ ሳይንቀሳቀስ እስካሁንም ቀጥሏል።

ለዚህም ነው ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለ12ኛ ጊዜ ስብሰባ የተቀመጠው ይላሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን።

የድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር አለማየሁ ዘውዴ፤ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው ይናገራሉ።

ሆኖም የተወሰኑ ኃያላን አገራትን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት ሲል በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ አካሄድ በመከተሉ ለሰብሰባ የተቀመጠበት ጊዜ በዝቷል ይላሉ።

"አገር አፈርሳለሁ" ብሎ በመነሳት ድንበር ጠባቂ ሰራዊትን ድንገት በማጥቃት ክህደት የጀመረና ጦርነት የከፈተ አሸባሪ ቡድን ጋር ህልውናዋን ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ እየተፋለመች ባለችበት ወቅት የምክር ቤቱ ጥያቄ ሌላ ሆኖ ተገኝቷል ይላሉ ዶክተር አለማየሁ።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን የውስጡን ባንዳ እና የውጪውን ሴራ በቅጡ በመረዳት ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳን በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት የራሳቸውን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ በኢትዮጵያ ተላላኪ መንግስት መመስርት ይሻሉ ያሉት ደግሞ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ዲን ዶክተር ጌታቸው ባዬ ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ያደረገው ተደጋጋሚ ስብሰባም የዚሁ ፍላጎት ነፀብራቅ መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ በርካቶች ሊበታትኗት ጥረው በህዝቦቿ ቆራጥ ትግል መዝለቋን ጠቅሰው የውጭውን ጫና እና ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ለመመከት ሁላችንም በጋራ የምንቆምበት ሌላኛው ወሳኝ ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቅ፤ የጋራ ቤታችን የሆነችውን አገር  ለመበታተን የሚመጡ ጠላቶችን በጋራ መመከት የኢትዮጵያዊያን የቆየ ልማድ መሆኑን ይናገራሉ።

አሁንም ቢሆን ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት እንዲሁም ህልውና የምንተባበርበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም