የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥርዓቱን በመፈተሽና የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ በመከተል ጫናውን መቋቋም ይገባል

95

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 12/2014(ኢዜአ) የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥርዓቱን በመፈተሽና የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ በመከተል ጫናውን መቋቋም ይገባል ሲሉ በደቡብ አፍሪካ የሱዋኔ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሙላቱ ፍቃዱ ገለጹ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድንና የሽብር ቡድኑን የሚደግፉ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ ጣልቃ ገብነትና ጫና እያሳደሩ መሆናቸው ይታወቃል።

የአገራቱ ጫና ከምን የመነጨ ነው? ይህንን ጫናስ እንዴት መቋቋም ይቻላል? ምን አይነት የፖሊሲ አማራጮችስ መወሰድ አለበት? የሚለውን የምሁራን ምልከታዎች አሉ።

በደቡብ አፍሪካ የሱዋኔ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ፕሮፌሰር ሙላቱ ፍቃዱን ኢዜአ በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል።

በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ጫናዎች በህዝቡ ላይ ከፍተኛ የስነ-ልቦና ጦርነት ለማምጣት የሚደረጉ መሆናቸውን ያነሱት ፕሮፌሰር ሙላቱ ይህ ጫና አሁን ላይ የመጣ ሳይሆን ቀደም ብሎም እንደነበር ያብራራሉ።

በአሁኑ ወቅት ጦርነቱን ተከትሎ የመጣውን ጫና ለመቋቋም የሚያስችሉ አማራጮችን በማስፋት ከመንግስትና ህዝቡ የተጠናከረ ስራ እንደሚጠበቅም ምክረ-ሐሳብ አንስተዋል።

በተለይም ቀድሞ የኢትዮጵያ ወዳጆች የነበሩና አሁን አገሪቱ ላይ አላስፈላጊ ጫና ለማሳደር ሲሉ በራቸውን ከዘጉ የአሜሪካ መንግስትና አንዳንድ አውሮፓውያን የሚደርሰውን ጫና ለመመከት የዲፕሎማሲ አማራጩን ማስፋት ይገባል ብለዋል።

ከሌሎች አገሮች ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ለመገንባት ሥራዎችን ማጠናከር ይገባልም ነው ያሉት።

በዚህም አሁን ላይ መንግሥት ከሌሎች አገሮች ጋር እየፈጠረ ያለው መልካም ግንኙነት ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ትልቅ እገዛ የሚያደርግ እንደሆነም አብራርተዋል።

ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ለማስቻልም በአገሪቱ ያለውን የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥርዓት መፈተሽ ይገባል ብለዋል።

ፖሊሲዎችን፣ ህጎችን፣ መመሪያዎችን እና አጠቃላይ የአሰራር ሂደቶችን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር መቃኘት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ወቅቱን በሚዋጅ መልኩ የመልሶ ግንባታ ቅደም ተከተልን ማስቀመጥ እንዲሁም ወቅቱን ተከትሎ የመጡ ችግሮችና ተግዳሮቶችን መቋቋም የሚያስችሉ የመልሶ ግንባታ እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሃብቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል እና የሰው ኃይሉን አንድ ላይ በማቀናጀት ጫናውን ለመቋቋም ትልቅ አቅም የሚፈጥር እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ መንግሥት፣ ምሁራን እና ሁሉም ዜጎች አስተዳደራዊና ሙያዊ እገዛ ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት ሁሉን አቀፍ ዘመቻ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረውን ጫና መቋቋም የሚያስችሉ የአጠቃላይ (ማክሮ) ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን መንግስት እየወሰደ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም