የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ለተፈናቀሉ ወገኖች ያሰባሰቡትን ምግብና አልባሳት ወደ ስፍራው ላኩ

71

ዲላ ታህሳስ 12/2014 (ኢዜአ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት በአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ህወሀት ለተፈናቀሉ ወገኖች ያሰባሰቡትን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና አልባሳት ድጋፍ ዛሬ ወደ ስፍራው ላኩ።

የማህበረሰብ አባላቱ በአሸባሪው ቡድን የወደመን ንብረት ለመተካትና የተፈናቀሉትን ለማቋቋም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ ዛሬ ድጋፉን በላኩበት ወቅት እንዳሉት በአሸባሪው ህወሀት ተፈናቅለው ለተቸገሩ ወገኖች መድረስ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት ነው።

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ካለው ላይ በማካፈል ከአፋርና አማራ ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ያሳየው ተነሳሽነት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።

ድጋፉም የጤፍ ዱቄት፣ ሩዝ ፣ብርድ ልብስ፣ ማዳበሪያ፣ የተለያዩ አልባሳትና እንዲሁም የሴቶች ንጽህና መጠበቂያን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ድጋፉ ከ1 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው መሆኑን ጠቁመው በጥፋት ሃይሎች የወደሙ ተቋማት ንብረቶች  እስኪተኩና የተፈናቀሉ ወገኖች እስኪቋቋሙ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ከየአቅጣጫው የተደቀነባትን አደጋ በድል እስክትሻገር ድረስ በጽናት መቆም እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሰራተኛ አቶ ይመኑ ዳካ ናቸው።

በተለይ አሸባሪው ህወሓት ያፈናቀላቸውን ከማቋቋምና የወደመውን ንብረት ከመተካት ባለፈ ኢትዮጵያን በተራዘመ ጦርነት በማዳከም እጅ ለመጠምዘዝ የሚሰሩ የውስጥና የውጭ ሃይሎችን በጋራ መመከት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም