የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ

290

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 12/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ፡፡

የኮርፖሬሽኑ አመራርና ሰራተኞች በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከዚህ ቀደም ድጋፍ አድርገዋል።

በዛሬው እለት ደግሞ ለአገር መከላከያ ሰራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ መደረጉን በኮርፖሬሽኑ የማህበራዊ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ትእግስት አለማየሁ ተናግረዋል።

የተቋሙ ሰራተኞች የአገር ሉአላዊነት እያስከበረ ላለው ሰራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች አጋርነታቸውን ለማሳየት በራሳቸው ተነሳሽነት ድጋፉን ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።

የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች በመጀመሪያው ዙር ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ሃላፊዋ አስታውሰዋል።

በቀጣይም ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።