ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ምርት የሚሰጠውን የስኳር ድንች ዝርያን ለአርሶ አደሮች እያስተዋወቀ ነው

149

ሐረር፤ ታህሳስ 12/2014 (ኢዜአ)፡ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በቫይታሚን ኤ ንጥረ ነገር የበለፀገውንና ከፍተኛ ምርት የሚሰጠውን የስኳር ድንች ዝርያን ለአርሶ አደሮች እያስተዋወቀ መሆኑን አስታወቀ።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለአርሶ አደሮች እያስተዋወቀ ያለው የስኳር ድንች ዝርያን ድርቅና የዝናብ እጥረትን ተቋቁሞ በቆላማ አካባቢዎች ከፍተኛ ምርት የሚሰጥና ቫይታሚን ኤ በተሰኘው ንጥረ ነገር  የበለፀገ ነው።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  የስኳር ድንች ተመራማሪ አቶ መሐመድ አብነሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዓለም አቀፍ የድንች ምርምር ማዕከል ጋር  በመተባበር በሐዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የተለቀቀ  ነው።

ተመራማሪው እንዳሉት  ይኸው “ብርቱኳናማ የስኳር ድንች” የሚል ስያሜ የተሰጠው ዝርያ ድርቅና የዝናብ እጥረትን ተቋቁሞ ከነባሩ ዝርያ በተሻለ በሄክታር እስከ 400 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ነው።

 ይኸው “ብርቱኳናማ የስኳር ድንች” ከነባሩ የስኳር ድንች ዝርያ በእጥፍ ብልጫ ያለው ምርት ከመስጠቱም ባሻገር በምግብ ንጥረ ነገር ይዘትም የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።  

በምግብ ይዘቱ በቫይታሚን ኤ የበለፀገ በመሆኑ በተለይ  ለሴቶች እና ህጻናት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም አመልክተዋል።

ይህ አዲሱ የስኳር ድንች ዝርያ በምዕራብ እና ምስራቅ ሐረርጌ፣ በድሬዳዋ እና ሐረሪ ክልል በሚገኙ 15 ወረዳዎች ውስጥ የማላመድ እና የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም  ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ የድንች ምርምር ማዕከል እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከአርሶ አደሩ፣ ምርጥ ዘር አምራቾች ማህበራትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዝርያውን የማስፋፋት የማላመድ ስራ እያከናወኑ ነው ብለዋል።

ብርቱካናማ የስኳር ድንች ዝርያን የማስተዋወቅ ስራ ባለፈው ዓመት በአንድ ቆላማ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ላይ መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ንጋቱ ናቸው።

የድንችዝርያው በአርሶ አደሩ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ በአሁኑ ወቅት ወደ 12 ቆላማ ቀበሌዎች ላይ የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ  ነው ብለዋል።

ይህ የስኳር ድንች ዝርያ የዝናብ እጥረትን ተቋቁሞ ከፍተኛ ምርት መስጠት እንደሚችል በተግባር የተረጋገጠ በመሆኑ ዝርያውን የማስተዋወቁና የማሰራጨት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስረድተዋል።

ከምርታማነቱም ባሻገር በቫይታሚን ኤ የበለጸገ በመሆኑ ከነባሩ የስኳር ድንች ዝርያዎች ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

የባቢሌ ወረዳ ኢፋ ቀበሌ ገበሬ ማህበር አርሶ አደር አብዲ ኡመር  ብርትኳናማ የስኳር ድንች ምርጥ ዘርያ  በቆላማ ቦታ ላይ ምርት የሚሰጥ መሆኑን  አልምተው በተግባር ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

''በትንሽ መሬት ከፍተኛ ምርት የሰጠኝን ብርትኳናማ የስኳር ድንች ዝርያን በአሁኑ ወቅት ከማስፋፋት ባለፈ ለሌሎች አርሶ አደሮች ዝርያውን እያሰራጨሁ እገኛለሁ'' ብለዋል።

ከቢሻን ባቢሌ ቀበሌ ገበሬ ማህበር አርሶ አደር አህመድ ሙስጠፋ በበኩላቸው አዲሱ የድንች ዝርያ በዝናብ እጥረት ምርት መስጠቱ ብቻ ሳይሆን ጣፋጭና ቫይታሚን ያለው በመሆኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጣቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል።

 ''በተለያየ የምግብ ዓይነት አድርገን የምንመገበው እና ጠቀሜታውም የጎላ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ተፈላጊነቱ ጨምሯል እኛም ቴክኖሎጂውን እያስፋፋን እንገኛለን'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም