በባሮ አኮቦ -ሶባት ተፋሰስ በዓመት ከ21 ሺህ ቶን በላይ ዓሳ ማምረት ይቻላል-ኢጋድ

99

ጋምቤላ ታህሳስ 12/2014(ኢዜአ)በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን የባሮ አኮቦ-ሶባት ተፋሰስ ወንዝ በዓመት ከ21 ሺህ ቶን በላይ ዓሳ ማምረት እንደሚቻል የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት /ኢጋድ/አስታወቀ።

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት /ኢጋድ/ ኢኮፊሽ ፕሮጀክት አዘጋጅነት የሁለቱ ተፋሰስ አገሮች ባለሙያዎች በዓሣ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ ከትናንት ጀምሮ በጋምቤላ ከተማ እየመከሩ ነው።

በኢጋድ የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅና የብሉ ኢኮኖሚ አስተባባሪ ዶክተር እሸቴ ደጀን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አገሮቹን በተፋሰሱ ያለውን የዓሣ ሀብት በተቀናጀ መንገድ የሚጠቀሙበት ፕሮጀክት ተነድፏል።

ባለፈው ዓመት የተጀመረው ፕሮጀክት በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን የባሮ አኮቦ-ሶባት ተፋሰስ ያለውን የዓሣ ሀብት በተቀናጀና በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል ዝርዝር ጥናት ተካሄዶ ወደ ትግበራ መግባቱን ተናግረዋል።

በተፋሰሱ በተካሄደ ጥናት የዓሣ ሀብቱ የነበሩበት የገበያና የብክነት ችግሮች ከተለዩ በኋላ ወደ ልማት የሚገባበት ፕሮጀክት መቀረጹን አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ በሁለቱ አገሮች መካከል የኢኮኖሚ ቅንጅትን በዘላቂነት ለመፍጠርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶችን በፍትሃዊነት ለመጠቀም እንደሚያስችል አመልክተዋል።

መድረኩ፣ ባለሙያዎች ሀብቱን በዘላቂነትና በተቀናጀ አግባብ ለመጠቀም በተቀረጸው ፕሮጀክት አተገባበር እንዲመክሩና መረጃ እንዲለዋወጡ ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የዓሣ ሀብት ልማት ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሁሴን አበጋዝ በሁለቱ አገሮች የባሮ አኮቦ- ሶባት ተፋሰስ ሰፊ የዓሣ ሀብት ቢኖርም፤ በአግባቡና በተቀናጀ መልኩ ጥቅም ላይ ሳይውል መቆየቱን ተናግረዋል ።

"በተፋሰሱ በዓመት ከ21 ሺህ ቶን በላይ ዓሣ የማምረት አቅም ቢኖርም፤ እስካሁን እየተመረተ ያለው ሶስት ከመቶ የማይበልጥ ነው" ብለዋል።

በመሆኑም በተፋሰሱ ያለውን ሰፊ የዓሣ ሀብት የተፋሰሱ አገሮች በተቀናጀ መልኩ ለማስተዳደርና ለመጠቀም እንደሚያስችል አቶ ሁሴን አስታውቀዋል።

በደቡብ ሱዳን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር የብዝሃ ህይወትና የውሃ አዘል መሬት ጄኔራል ዳይሬክተር ሚስተር ጆን አተር ፕሮጀክቱ በሁለቱ አገሮች ድህነትን የሚቀንስና የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ መሆኑን አመልክተዋል ።

ፕሮጀክቱ ሀብቱን በተቀናጀ መልኩ ለረጅም ጊዜ ለመጠቀም እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ለአራት ቀን  በሚቆየው የባለሙያዎች የምክክር መድረክ ጥናታዊና በፕሮጀክቱ አተገባበር ሂደት ዙሪያ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም