በደሴና ኮምቦልቻ በአሸባሪው ህወሃት የተዘረፉ ኢንዱስትሪዎችን ዳግም ስራ ለማስጀመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተካሄደ

289

ታህሳስ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች በአሸባሪው ህወሃት የተዘረፉ ኢንዱስትሪዎችን ዳግም ስራ ለማስጀመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተካሄደ።

ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የሚመለከታቸው ተቋማት የስራ ሃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢንደስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ አሸባሪው ህወሓት በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት መፈፀሙን ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን በደሴና ኮምቦልቻ ወረራ በፈፀመበት ወቅት የግለሰቦችን ንብረት ጨምሮ በርካታ ኢንዱስትሪዎችን ዘርፏል ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ዓላማ በአገር ላይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ከማስከተል ባለፈ በባለሃብቶችና በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ የስነ ልቦና ጫና ለማሳረፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዘረፋቸው ኢንዱስትሪዎች ተመልሰው አገልግሎት እንዳይሰጡ በማውደም የህዝብና የአገር ጠላት መሆኑን በግልጽ አሳይቷል ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ኢንዱስትሪዎችን የጦር ካምፕ በማድረግ ጭምር ከፍተኛ ጉዳት አድርሶባቸዋል ነው ያሉት።

ውድመቱ የከፋ ቢሆንም የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ዳግም ስራ ለማስጀመር መረባረብን ይጠይቃል ብለዋል።

በመልሶ ግንባታ አንዳንዶች ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመው፤ ስራ ለመጀመር በሂደት ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉም አቶ መላኩ ገልጸዋል።

አጠቃላይ ኢንዱስትሪዎችን በሂደት ወደ ስራ ለማስገባት የሁሉም እገዛና ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።