አሸባሪው ህወሓት በራያ ቆቦ ከተማ ከ120 በላይ ንጹሃንን በጅምላ ጨፍጭፏል

265

ታህሳስ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በራያ ቆቦ ከተማ ከ120 በላይ ንጹሃንን በጅምላ መጨፍጨፉን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሓት በወረራ ገብቶባቸው በነበሩ የአማራ እና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ንጹሃንን በጅምላ ከመግደል በተጨማሪ ከፍተኛ የንብረት ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል።

አሸባሪ ቡድኑ በራያ ቆቦ ከተማ በቆየባቸው ጊዜያት ንጹሃንን ያለ ርህራሄ ጨፍጭፏል፤ ነፍሰ ጡርን ጨምሮ በርካታ ሴቶችን መድፈሩንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም የማይገባውን ግፍ እና መከራ በከተማው ነዋሪዎች ላይ መፈፀሙንም የአይን እማኞች ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በራያ ቆቦ ከተማ ከ120 በላይ ንጹሃንን በጅምላ በመጨፍጨ አረመኔነቱን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

ከዚህ በፊት አሸባሪ ቡድኑ በቆቦ ከተማ ላይ ከፍተኛ በደል ሲፈጽም መቆየቱን ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፤ የዘጠኝ ወር ነብሰ ጡርን ጨምሮ በርካታ ሴቶችን አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ አሁንም የጭካኔ በትሩን ማሳረፉን ጠቁመዋል።

ቡድኑ ወንዶች ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸሙን ጠቅሰው፤ የቡድኑ ታጣቂዎች ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ንብረት መዝረፍና ማውደምን ጨምሮ ያልፈጸሙት ግፍ እንደሌለ ተናግረዋል።

በርካታ የከተማው ነዋሪዎችን በአደባባይ ያለ ርህራሄ በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉን የአይን እማኞች ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ጥምር ጦሩ አሸባሪውን ቡድን በመደምሰስ አካባቢውን ከወራሪው ነጻ በማውጣቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።