የኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ ሂደት በአፍሪካዊያን ላይ የተከፈተ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ትግል ነው

86

ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ ሂደት በአፍሪካዊያን ላይ የተከፈተ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ትግል በመሆኑ ህዝቡ በጋራ ክንዱ እየመከተው ነው።

የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የጥናትና ምርምር ምክትል ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ፤የውስጥ ባንዳዎች ከውጭ ጠላቶች ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የከፈቱት ጦርነት በቆራጥ ልጆቿ እየተመከተ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት በአገር ህልውና ላይ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ኢትዮጵያዊያን ከዳር ዳር በመነሳት በድጋፍም በመዋጋትም ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ የታሪክ አጋጣሚ በጀግንነት እየተፋለመ ያለው ሰራዊት የአገሩን ክብርና ሉአላዊነት እያስጠበቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የድርሻውን ለመወጣት ለአገር መከላከያ ሰራዊት የአልባሳትና የጽዳት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ዶክተር ተመስገን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ ሂደት በአፍሪካዊያን ላይ የተከፈተ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ትግል በመሆኑ ህዝቡ በጋራ ክንዱ እየመከተው ነው ብለዋል።

በቅኝ ግዛት ትግል አሸናፊ በመሆን የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ ለእጅ አዙር ቅኝ ግዛትም እጅ የማትሰጥ አገር መሆኗን በተግባር እያሳየች ትገኛለች።

አርቲስት ደበበ እሸቱ ደግሞ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ያሰባሰበውን አልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለሰራዊቱ አስረክቧል።

ለኢትዮጵያ ህልውና መስዋእትነት እየከፈለ ላለው ሰራዊት የምናደርገው ድጋፍ አጋርነታችንን ለማሳየት እንጂ ብዙ ሆኖ አይደለም ያለው አርቲስት ደበበ፤ በጀግንነት የአገራችንን ክብር በማስጠበቃቸው ኮርተናል ብሏል።

በመከላከያ ሰራዊት የዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሀብታሙ ጥላሁን፤ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ሰራዊት የተገነባበት ስነ ምግባር ከራስ በፊት ለሀገር በመሆኑ ለአገሩ ክብር ቆራጥ መስዋእትነት እየከፈለ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም