ለዘማች ቤተሰቦች የሚደረግ ድጋፍ የኢኮኖሚ ጫናን ከማቃለል ባለፈ ለዘመቻው ስኬት አስተዋጾ እንዳለው ተመለከተ

150

እንጅባራ፣ ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ ) ለዘማች ቤተሰቦች የሚደረግ ድጋፍ የኢኮኖሚ ጫናን ከማቃለል ባለፈ ለህልውና ዘመቻው ስኬት አስተዋጻው የጎላ መሆኑ ተመለከተ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  የባህርዳር ዲስትሪክት ሠራተኞች “አንድ የባንክ ሠራተኛ አንድ የጉልበት ሠራተኛ” በሚል መሪ ሃሳብ ባደረጉት የገንዘብ ድጋፍ በአዊ ብሔረሰብ ዞን የዘማች ቤተሰቦች ሰብል ተሰብስቧል።

የዲስትሪክቱ የ77 ቅርንጫፍ ሰራተኞች በግለሰብ ደረጃ 250 ብር በማዋጣት በብሔረሰብ ዞኑ ባንጃ ወረዳ ዚቕ ጎመርታ ቀበሌ ከ2 ሄክታር በላይ የዘማች ቤተሰቦች ጤፍ በጉልበት ሠራተኞች  እንዲሰበሰብ ማድረጋቸውን የዲስትሪክቱ የጥራት አስተዳደርና ቁጥጥር ስራ እስኪጅ አቶ አስቻለው ታከለ ለኢዜአ ተናግረዋል።

አቶ አስቻለው  በወቅቱ እንዳሉት ሠራተኞች የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብ ያደረጉት ድጋፈ ለህልውና ዘመቻው ውጤታማነት ያግዛል።

ለዘማች ቤተሰቦች በሰብል ስብሰባና በሌሎች የሚደረግ ድጋፍ በቤተሰቦች ላይ ሊከሰት የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ከማቃለሉ ባለፈ ግንባር ያለው ዘማች ትኩረቱን በወራሪው አድርጎ የህልውና ትግሉን በአጭር ጊዜ እንዲያጠናቀቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።

“የህልውና ዘመቻ ድጋፉ ከሰብል መሰብሰብ በተጨማሪ ግንባር ድረስ በመዝመት ህይወትን እስከመሰዋት የሚደርስ ነው”  ሲሉ አብራርተዋል።

የዲስትሪክቱ ሰራተኞች ባደረጉት ተመሳሳይ ድጋፍ በዞኑ ዳንግላ ወረዳ የሰብል ስብሰባ መካሄዱን አስታውሰዋል።

የዲስትሪክቱ ሠራተኞች በቀጣይ ሰብል የተነሳበት  ማሳ ታርሶ በዘር እንዲሸፈን  የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል ።

“ህብረተሰቡን እያገለገልን መደበኛ ስራችንን ሳይሻማ በገንዘባችን የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል እየሰበሰብን እንገኛለን” ያሉት ደግሞ የዲስትሪክቱ የአይሲቲ ባለሙያ አቶ ዕውነቱ አይቸው ናቸው።

“እያንዳንዳችን የአንድ የጉልበት ሠራተኛ የቀን ወጪ በመሸፈን የዘማች ቤተሰብ ሰብል በወቅቱና በአግባቡ እንዲሰበሰብ አድርገናል፣ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።

” የ212 የሚሊሻ ቤተሰቦችን የመንከባከብና ሰብል የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ ነው” ያሉት ደግሞ የባንጃ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ዳኛው ናቸው።

ህብረተሰቡ የዘማች ቤተሰቦችን መሬት በዘር ከመሸፈን ጀምሮ ሰብሉን የመንከባከብ ስራ ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ እየተደረገ ያለው ጥረት መቀጠሉን አመልክተዋል።

“ቀደም ሲል 20 ሄክታር የደረሰ የዘማች ቤተሰብ ሰብል ተሰብስቧል” ያሉት ኃላፊው በዛሬው እለትም የባንኩ ሰራተኞች ባደረጉት እገዛ ከ2 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የደረሰ የጤፍ ሰብል መሰብሰብሰቡን ተናግዋል።

“ባለቤቴ ሃገርና ህዝብ ለመጠበቅ ግንባር ቢሄድም በህብረተሰቡ እየተደረገልኝ ባለው ድጋፍ ኩራት ተሰምቶኛል” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አበባ አረጋ ናቸው።

 “የባለቤቴ መዝመት የሀገርን ህልውና ለመታደግ በመሆኑ ተገቢ ነው” ወይዘሮ አበባ ህብረተሰቡ እያደረገላቸው ላለው ሁለንተናዊ ድጋፍና እንክብካቤ አመስግነዋል።

በህብረተሰብ ድጋፍ  ከዚህ ቀደም ከግማሽ ሄክታር በላይ ማሳቸው ታርሶ በዘር መሸፈኑን አስታውሰው አሁን ላይ የደረሰ ሰብላቸውን  አጭዶ በመሰብሰብ እገዛ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል።

ወይዘሮ አየሁሽ ጌታቸውም ባለቤታቸው ግንባር ቢዘምቱም የህብረተሰቡ  እገዛና ክትትል እንዳልተለያቸው ገልጸዋል።

ባለቤታቸው ከዘመቱ ጊዜ ጀምሮ ግማሽ ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑንና  ለጤፍ ሰብላቸው ከእንክብካቤ እስከ ስብሰባ ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል ።