የበቃ /#No More/ እንቅስቃሴ የፓንአፍሪካኒዝም ጽንሰ ሐሳብን ለማስረፅ አበርክቶ አለው

158

ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ)የ”በቃ ወይም #No More” እንቅስቃሴ የፓንአፍሪካኒዝምን ጽንሰ-ሐሳብ ለማስረፅና የአፍሪካዊያንን አንድነት ለማጠናከር አስተዋፅኦ አለው ይላል አርቲስት ስለሺ ደምሴ /ጋሽ አበራ ሞላ/።

ስለ ኢትዮጵያ የሚሟገቱ ታዋቂ የውጭ አገራት ዜጎችን ልንጠቀምባቸው ይገባልም ብሏል።

አርቲስቱ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ “የበቃ ወይም #No More” እንቅስቃሴ በእያንዳንዱ አፍሪካዊ ልብ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የነበረ ስሜት መሆኑን ገልጿል።

በኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተጀመረው ይህ እንቅስቃሴ ለአፍሪካዊያን ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥርና የፓንአፍሪካኒዝምን ጽንሰ-ሐሳብ ለማስረጽ እንደሚረዳ ነው የተናገረው።

ኢትዮጵያም የጀመረችውን “የበቃ ወይም #No More” እንቅስቃሴን አጠናክራ መቀጠል አለባት ባይ ነው አርቲስቱ።

ኢትዮጵያዊያን “የበቃ ወይም #No More” ንቅናቄን ደግፈው የሚንቀሳቀሱ ታዋቂ የውጭ አገር ዜጎችን ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባልም ብሏል።

የውጭ አገር ዜጎች ስለ ኢትዮጵያ ድጋፍ መስጠታቸው የምዕራባዊያንን የመገናኛ ብዙኃን የሐሰት ዘገባ ለማጋለጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው አርቲስት ስለሺ ይናገራል።

በሌላ በኩል አርቲስቱ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ተፈናቃዮችን ለመደገፍ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ፕሮጀክት ማቀዱን ገልጿል።

ከመንግሥትና ከማኅበረሰቡ የተውጣጣ ኮሚቴ በማዋቀር ተፈናቃዮችን በገንዘብ መደገፍና የፈራረሱ አካባቢዎችን መልሶ ማልማት የሚቻልበትንም ሁኔታ ለማመቻቸት ማሰቡንም ተናግሯል።