በአማራ ክልል የወደሙ የፖሊስ ተቋማትን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው

217

ባህርዳር፣ ታህሳስ 11/2014(ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ሀይል በአማራ ክልል ያወደማቸውን የፖሊስ ተቋማት ወደ ሥራ ለማስገባት በትብብር እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደምመላሽ ገብረ ሚካኤል አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የቢሮ መገልገያዎችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለወደሙ የፖሊስ ተቋማት ስራ ማስጀመሪያነት ዛሬ በድጋፍ አበርክቷል።

ኮሚሽነር ጄኔራል ደምመላሽ በርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት ድጋፉ የተደረገው ከአሸባሪው ህወሓት ወረራ ነጻ የወጡ አካባቢዎች ፖሊስ ጣቢያዎች ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ነው።

ኮሚሽኑ ቡድኑ በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች መስዋዕት የሆኑ የፖሊስ አመራሮችና አባላትን በመዘከር ቀሪዎቹ የፖሊስ አመራሮችና አባላት ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት  በኩባንያቸው መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል።

የኩባንያቸው ሠራተኞችም በአሁኑ ወቅት የወገን ጥምር ጦር ድል ባስመዘገበባቸው አካባቢዎች የቴሌኮም መሰረተ ልማትን በመጠገን አገልግሎት እያስጀመሩ መሆኑን ተናግረዋል።

“የፖሊስ ጣቢያዎች ልክ እንደኛ መሠረተ ልማት ውድመት ደርሶባቸዋል” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወደ ቀያቸው የሚመለሱ ዜጎች አገልግሎት እንዲያገኙ ለ83 ጣቢያዎች የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ እንዳሉት አሸባሪው ቡድን በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ የመንግሥት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ አውድሟል።

“ይህም አሸባሪዎች አካባቢዎቹ ነጻ ሲወጡ የመንግሥት ዋና ተግባር የሆነውን የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ተግባር በአግባቡ እንዳይወጣ ባላቸው እኩይ ዓላማ መሰረት የፈጸሙት አስነዋሪ ተግባር ነው ” ሲሉ አስረድተዋል።

ተቋማቱ ባደረጉት ትብብር በአካባቢዎቹ ለሰላምና ደህንነት መከበር መሠረት የሆነውን የፖሊስ አገልግሎት ለማስጀመር  እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ አሸባሪው ህወሃት በክልሉ በአምስት ዞኖች የሚገኙ መምሪያዎችንና በ78 ወረዳዎች የሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎችን ሙሉ በሙሉ እንዳወደመ ተናግረዋል።

ተቋማቱ በመውደማቸው አሁን ነጻ በወጡ አካባቢዎች የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠት ችግር ማጋጠሙን አመልክተዋል።

ኮሚሽኑና ኢትዮ ቴሌኮም ያደረጉት ድጋፍ የፖሊስ አገልግሎትን ወደ ሥራ ለማስገባት እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ድጋፉ 200 ኮምፒዩተሮች፣ 100 ፕሪንተሮች፣ 200 ጠረጴዛዎች፣ 200 ወንበሮች፣ 50 የእንግዳ መቀበያ ወንበሮች፣የመመገቢያና የመገልገያ ቁሳቁሶችን ያካተተ ስለመሆኑ በርክክብ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።