የተፈናቀሉን ለማቋቋም የታየው ርብርብ አገርን በሚያሻግሩ ሌሎች መስኮች መጠናከር አለበት- አቶ አወል አርባ

67

ሰመራ፣  ታህሳስ 11/2014(ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም የታየው ርብርብ አገርን በሚያሻግሩ ሌሎች መስኮች መጠናከር እንዳለበት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አመለከቱ።

የአማራ ልማት ማህበርና ግሎባል አላያንስ በአሸባሪው ህወሀት በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች በጥሬ ገንዘብና በአይነት የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ዛሬ ለክልሉ አስረክበዋል።

የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሸባሪው ህወሀት ወረራ ለተጎዱ ወገኖች እያደረገ ያለው ድጋፍ ኢትዮጵያዊ መረዳዳትና መደጋገፍን አጉልቶ አሳይቷል።

"ይህንን አኩሪና ዘመናት የተሸጋገረ ባህልና ልምድ አገርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር በሚያስችሉ መስኮች ማስቀጠል ያስፈልጋል" ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን በአሸባሪው ቡድን ወረራ ችግር ውስጥ ለወደቁት ወገኖቻቸው ያደረጉት ድጋፍ አኩሪ መሆኑን አመልክተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ተቋማቱ ለተፈናቃዮች ላደረጉት ድጋፍ በክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ከድጋፉ በጥሬ ገንዘብ 5 ሚሊዮን ብር ያበረከተው የአማራ ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ ማህበሩ የአፋርና አማራ ክልል ሕዝቦች የቆየ የመረዳዳትና መደጋገፍ አኩሪ ባህል እንዳላቸው ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን በሁለቱ ክልሎች በከፈተው ጦርነት ህዝቦች ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።


ማህበሩ ከአፋር ህዝብ ጎን በመቆም ተፈናቃዮች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።

የግሎባል አላያንስ የቦርድ ሰብሳቢ አርቲስት ታማኝ በየነ በበኩሉ በወረራው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ መደረጉን ተናግሯል ።

ድጋፉ የወገኖቻችንን ችግር በመጠኑ ያቃልላል በሚል እሳቤ  የተደረገ ነው" ያለው አርቲስቱ ወደ ፊትም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጨማሪ ድጋፍ ለማሰባሰብ እንደሚሰራ አስታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም