በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት የባለሃብቶች ተነሳሽነት አበረታች ነው

188

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ)በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት በባለሃብቶች ዘንድ እየታየ ያለው ተነሳሽነት አበረታች መሆኑ ተገለጸ።

የሽብር ቡድኑ ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በርካታ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፣የሕዝብ መገልገያ ተቋማትና የግለሰብ ንብረትም በመዝረፍ በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ሠብዓዊ ጉዳት አድርሷል።

በመሆኑም ቡድኑ ያወደማቸውን መሰረተ ልማቶችና የሕዝብ መገልገያ ተቋማት መልሶ ለመገንባት መንግስትና ባለሃብቶች እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።

የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጋር መቀናጀት ይገባል ይላሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ባለሃብቶች።

ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገውና በግል ስራ የሚተዳደረው ቤን መርዕድ ጦርነቱን ‘ኢትዮጵያዊያንን አንድ ያደረገ’ ሲል ገልጾታል።

በዚህ አንድነት በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት እየታየ ያለው ተነሳሽነት የሚያበረታታ እንደሆነም ነው የተናገረው።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የወደሙ የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ የአገር ውስጥ ባለሃብቱ የማጓጓዣ ወጪውን ቢሸፍን መልሶ ግንባታው ይፋጠናል ብለዋል።

የዱከም ራዳር ሆቴል ባለቤት ወይዘሮ እመቤት ይልማ በበኩላቸው ከጦርነቱ ባሻገር አገሪቷ የገጠማትን የኢኮኖሚ ጦርነት ለመወጣት ባለሃብቱም፣ሌላውም ኅብረተሰብ በአንድነት መቀናጀት አለበት ነው ያሉት።

በጠቅላይ ሚኒስትር አቢህ አህመድን ጥሪ መሰረት ወደ አገር ቤት የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ገንዘባቸውን በጥቁር ገበያ ባለመመንዘር አገር ወዳድነታቸውን እንዲያሳዩም ጭምር አደራ ብለዋል።